የአማራ ክልል የኢኮኖሚ ጭቆና እየተደረገበት ነው ተባለ

0
772

የአማራ ክልል የምጣኔ ሀብት ጭቆና እየተደረገበት መሆኑን ከሐምሌ 12/2015 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ሲያካሂድ የቆየው የክልሉ ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የመንገድ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የኔትወርክ እና ሌሎች መሰረተ ልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ “ነገር ግን የክልሉ መንግሥት ከወሬ በዘለለ እስካሁን ባለበት እየተጓዘ ነው።” ሲሉ ተደምጠዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን ከፍተኛ የአፈር ማዳበሪያና የምርጥ ዘር እጥረት መኖሩም በቀጣይ ዓመት እስከ 50 በመቶ የሚደርስ የምርት መቀነስ ሊያስከትል እንደሚችልና ይህም የጎላ ቀውስ እንደሚያስከትል ጠቁመዋል።

እንዲሁም በክልሉ ይገነባሉ ተብሎ ከ20 ዓመት በፊት የታቀዱ ትላልቅ የመንገድ፣ የመስኖ፣ የማኑፋክቼሪንግ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች መረሳታቸውን የጠቁሱት የምክር ቤት አባላቱ፣ እነዚህ ኹሉ ክልሉ የምጣኔ ሀብት ጫና እየተደረገበት መሆኑን ማሳያ ናቸው ብለዋል።

አዲስ አበባ ካሏት አምስት መግቢያና መውጫ በሮች የአማራ ሕዝብ የሚገባባቸው ኹለቱ ብቻ የሚዘጉ መሆኑም የክልሉ ሕዝብ እና ተወላጆች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚደርስባቸውን ጫና የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ስለሆነም የአማራ ሕዝብ የምጣኔ ሀብት፣ የማህበራዊ እና የፖለቲካ አገልግሎት እንዳያገኝ ጫና እየተደረገበት መሆኑ ነው በምክር ቤቱ የተጠቆመው።

በተጨማሪም የአማራን ሕዝብ አንገት ለማስደፋት በተግባር የሚገለጡ ቀን ከሌሊት የሚደረጉ ሩጫዎች መኖራቸው ተመላክቷል።

ስለሆነም ሕዝቡ ችግር የለበትም ያሉት የምክር ቤት አባላቱ፤ የክልሉን ችግር ለመፍታት ቅድሚያ መዋቅሩን እናስተካክል ሲሉ ተደምጠዋል።

በብዙ ቦታዎች ከመጠን ያለፈ የሰላም ችግር መኖሩን በማንሳትም፤ አሁን ላይ ያለውን የሰላም ችግር በውይይት መፍታት እንደሚገባ እና ክልሉም በጉዳዩ ላይ በደንብ መምከር እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ ርዕስ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ “ችግሩን በራስ የመፍታት አቅም መፍጠር አለብን” ሲሉ ገልጸው፤ “አማራ ክልል ላይ ያለው ጥያቄ ምንድን ነው? የሚለው መፈተሽ አለበት።” ብለዋል።

በክልሉ ያለውን ችግር ለመፍታትም በየዞኑ ከምክር ቤት አባላት አምስት አምስት ሰው ተምርጦ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽመግሌዎች፣ ምሁራንና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የተሳተፉበት ውይይት ያለምንም ገደብ እንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here