በጋምቤላ ክልል ለሚፈጠረው ግጭት የክልሉ መንግሥት ተጠያቂ ነው ተባለ

0
577

በጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ እየተፈጠረ ላለው ግጭት፤ የክልሉ መንግሥት ተጠያቂ መሆኑን የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ሳይመን ቱት፤ “በክልሉ በሚገኙ የኑዌር እና አኝዋክ ብሄረሰቦች መካከል በየጊዜው የሚፈጠረውን ግጭት እያባባሱት ያሉት የክልሉ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችና የከተማ መስተዳድሩ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡

በዚህም ሰኞ ሐምሌ 17/2015 አስር ሰዓት አካባቢ በኢታንግ ልዩ ወረዳ ሁልዴን በተባለ ቀበሌ በተቀሰቀሰ ግጭት 12 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል።

“ግጭቱ እየተካሄደ ያለው “በቀል እንመልስ” በሚል በኹለቱ ብሄረሰቦች መካከል ነው፡፡” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ በውጊያው ላይ የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ሳይቀር ተሳታፊዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የሚገኙ የፖሊስ አባላት አብዛኞቹ የአኝዋክ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው፤ በኑዌር ብሔረሰቦች ላይ ጥቃት እየሰነዘሩ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በኹለቱ ብሔረሰቦች መካከል በሚደረግ ተደጋጋሚ ግጭቶች በተለይ በርካታ ሕጻናት፣ እናቶችና አዛውንቶች መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም፤ “ጋምቤላ ክልል ላይ የሚፈጠረውን የብሔር ግጭት መንግሥት ራሱ እንደመሳሪያ እየተጠቀመው ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ብዙ ጊዜ ችግር የሚፈጠረው ኹሉም ብሄረሰቦች በብዛት በሚገኙበት በኢታነግ ልዩ ወረዳ መሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ “የኑዌር ብሔረሰቦችን ስደተኞች ናቸው በማለት ከፍተኛ ጭቆና እተደረገባቸው ነው፡፡” ሲሉም ተናግረዋል።

ሐምሌ 11/2015 አስር ሰዓት አካባቢ የአኝዋክ ብሔረሰቦች በሰነዘሩት ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰውም፤ “በዚህም ከተገደሉት መካከል 17ቱ የኑዌር ብሔረሰብ አባላት ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡

እንዲሁም ሐምሌ 13/2015 በኢታንግ ልዩ ወረዳ ፒኖ ተብሎ በሚጥራ ቦታ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነው የጠቆሙት።

በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ለፌደራል መንግሥቱ ትክክለኛ መረጃ እየሰጠ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩ በኹለቱ የብሔረሰብ አባላት የስልጣን ሽኩቻ ጋር የተያያዘ በመሆኑና መንግሥት እርምጃ ባለመወሰዱ የጸጥታ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here