ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት መጠን ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆሉን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ግዛት ወርቁ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ለዓለም ገበያ ያቀረበችው የቡና መጠን 302 ሺሕ ቶን መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ ዓመት ግን 240 ሺሕ ቶን ብቻ ማቅረቧን እና ይህም ከባለፈው ዓመት ለዓለም ገበያ ከቀረበው የቡና ምርት ጋር ሲንጻጸር በ62 ሺሕ ቶን መቀነሱን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ አክለውም፤ ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት ለዓለም ገበያ ካቀረበችው ቡና 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘቷን እና ይህም ከባለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነጻጸር በ90 ሚሊዮን ዶላር መቀነሱን ገልጸዋል።
ቡናን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ግንባር ቀደም የሆነችው ብራዚል ባለፈው ዓመት በተከሰተ ውርጭ እና ድርቅ ምክንያት የቡና አቅርቦቷ ቀንሶ እንደነበር በመጠቆም፤ ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው የቡና መጠን ከፍ ብሎ እንደነበር ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው በጥራት መለኪያ ደረጃ አምስት የተሰኘ ቡና በኪሎግራም በ3 ነጥብ 46 ዶላር ወይም 190 ብር እንደሚሸጥ የተጠቆመ ሲሆን፤ ይህም ትርፍ እንደማያስገኝ እና አክሳሪ መሆኑ ተመላክቷል።
ይኸው ቡና በአገር ውስጥ በገበያ ኪሎ ግራም 400 ብር እንደሚሸጥ የጠቀሱት የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ፤ ላኪዎቹ ቡናውን ውጭ ገበያ ላይ ከሚሸጡበት በበለጠ ዋጋ ከአገር ውስጥ ገበያ ገዝተው በመላክ፣ በምትኩ ሌሎች ዕቃዎችን በማስገባት ኪሳራቸውን እንደሚያካክሱ አስገንዝበዋል።
ይህም የአገር ውስጥ ምርትን በውድ ዋጋ ገዝቶ ለዓለም ገበያ በርካሽ ማቅረብ ለዋጋ ግሽበት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።
ስለሆነም መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ሕገወጥነትን በማስተካከል ፖሊሲዎችን አሻሽሎ ነገሮችን ማስተካከል እና ወደ መስመር ማስገባት ካልቻለና በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የቡና ገበያው ወዳልሆነ አቅጣጫ መሄዱ አይቀርም ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ገበያ በቂ የቡና አቅርቦት መኖሩም ለቡና ዋጋ መውረድ ዋነኛ ምክንያት ነው ተብሏል።
እንዲሁም ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ ሰዎች እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አለመቻላቸው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ምርቱ ወዳለበት ቦታ ሄደው ቡና በሚለቀሙ ሠራተኞች ላይ በፈጠረው ችግር፤ የቡና ምርቱን በወቅቱ ለመልቀም አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን እና በምርት ጥራቱ ላይም ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡



