በጎንደር ደባርቅና መተማ ከተሞች በርካታ የሱዳን ስደተኞች መኖራቸው ተገለጸ

0
778

ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ጎንደር፣ ደባርቅና መተማ ከተሞች በርካታ የሱዳን ስደተኞች እንደሚገኙ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡

በዚህም በተለይ ጎንደር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች ከሱዳን በመጡ ስደተኞች ለረዥም ጊዜ ኮንትራት ተይዘዋል ነው የተባለው።

ለአብነትም ሰሞኑ የ12ኛ ክፍልን ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡ ከአንድ ሺሕ በላይ መምህራን የሚያድሩበት አልጋ አጥተው መቸገራቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

እንዲሁም በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ እና በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ከተማ በርካታ የሱዳን ስደተኞች መኖራቸው ተገልጿል።

በተጠቀሱት ከተሞች አቅም ያላቸው ስደተኞች አልጋ ይዘውና ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ አቅም የሌላቸው ሱዳናዊያን ደግሞ ለጎዳና ሕይወት እና በከፋ ችግር መጋለጣቸው ተመላክቷል።

ከሱዳን ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ኢትዮጵያን በአንጻሩ በየዘመዶቻቸው የተጠለሉ ቢሆንም፤ ሱዳናዊያን ስደተኞች ግን የሚያስጠልላቸው አጥተው ለጎዳና ተዳርገዋል ነው የተባለው።

በከተሞቹ የስደተኞቹ መብዛት የጸጥታ ችግር ስጋት መፍጠሩንም ነዋሪቹ ጠቅሰዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ ላሉ ስደተኞች የትራንስፖርት፣ የምግብ፣ የውሃ እና በአጠቃላይ የሕይወት አድን አገልግሎቶችን በበቂ ሁኔታ ማግኘት ባለመቻላቸው ችግር ላይ ናቸው ብሏል።

በተጨማሪም በአካባቢው በሚጥለው ዝናብ ሳቢያ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሠራተኞች በተፈለገው መጠን ወቅታዊ ድጋፍ እየሰጡ አለመሆኑም ነው የተገለጸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ በግጭት ከምትታመሰዋ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሰዎች ቁጥር ከ68 ሺሕ በላይ መደረሱን አስታወቋል፡፡

የሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ እስከ ሐምሌ 13/2015 ድረስ 68 ሺሕ 601 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ያለው ተቋሙ፤ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት አጠቃላይ ስደተኞች መካከል 49 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵዊያን ሲሆኑ 30 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሱዳናዊያን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና የቅድመ ማሰጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር ብርሃኑ ዘወዱ ብትደውልም፤ ስብሰባ ላይ ነኝ በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here