ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ተፈናቅለው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው የሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
በዚህም ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ከመንግሥትም ሆነ ከተለያዩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ምንም ዓይነት ሰብዓዊ ድጋፍ እያገኙ አይደለም ማለቱን አዲስ ማለዳ ድርጅቱ ካወጣው መግለጫ ላይ ተመክታለች።
በአሁኑ ወቅትም ተፈናቃዮቹ ባሉባቸው አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ተግዳሮት መሆኑን ነው ድርጅቱ የገለጸው።
በ2021 እና 2022 የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ በጸጥታ ችግር ምክንያት ከምስራቅ ወለጋ ጎቡ፣ ሰዮ እና ዋዩ ወረዳዎች 13 ሺሕ 800 ሰዎች መፈናቀላቸውን እና በአካቢው ባሉ ሰዎች እርዳታ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
ተፈናቃዮቹ ምንም ዓይነት አገልግሎት ካለማግኘታቸው በተጨማሪ በአካባቢው ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ምክንያት ካሉበት የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ወጥተው መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ተገልጿል፡፡
ተፈናቃዮች ከፍተኛ የሆነ የምግብ፣ የሕክምና አገልግሎት ችግር እጋጥሟቸዋል ያለው ድርጅቱ፤ የክልሉ መንግሥት ባለፈነው ሰኔ ወር ከ45 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የስንዴ ዱቄት ድጋፍ ቢያደርግም ተደራሽነቱ ግን ሰባት በመቶ ብቻ ነበር ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በባሌ ዞን ሀረና ቡሉቅ ወረዳ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ በአሁን ወቅት በኦሮሚያ፣ በሲዳማ፣ ሶማሌ፣ በደቡብ ክልሎች ባሉ 69 ወረዳዎች መስፋፋቱ የተገለጸ ሲሆን፤ እስከ ሐምሌ 12/2015 ድረስ በተሰበሰበው መረጃ 257 ተፈናቃዮች እና 13 ሺሕ 700 ሰዎች በበሽታው የተያዙ መያዛቸውንና 179 ሰዎች መሞታቸውን ተመድ በሪፖርቱ አመላክቷል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች የተነሳ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቀሳል።



