በመቀሌ ከተማ ሰልፍ የወጡ ከስድስት ሺሕ በላይ አካል ጉዳተኛ የሕወሓት ታጣቂዎች በፖሊስ ኃይል መበተናቸው ተገለጸ

0
1187

ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትናንትናው ዕለት በመቀሌ ከተማ ድጋፍ እንዲደረግላችው እና ጥቅማ ጥቅም እንዲከበርላቸው ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የተሰባሰቡ ከስድስት ሺሕ በላይ አካል ጉዳተኛ የሕወሓት ታጣቂዎች፤ በፖሊስ ኃይል እንዲበተኑ መደረጋቸውን ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ወደ ተለያዩ የክልሉ ቦታዎች ተመልሰው ከቤተሰቦቻቸው በሚደረግላቸው ድጋፍ የሚኖሩ ከስድስት ሺሕ በላይ በጦርነቱ ወቅት ቆስለው የአካል መጉደል ያጋጠማችው ወጣቶች፤ በመቀሌ ከተማ ሃያ ኹለት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን እና ፖሊስ ሠልፈኞቹን በኃይል እንዲበተኑ ማድረጉን የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ አደራጅ ጊደሰና መድኅን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፓርቲው አደራጅ አክለውም፣ ከዚህ ቀደም በሕወሓት ሥር ተመዝግበው ከሚገኙ 274 ሺሕ ታጣቂዎች መካከል 50 ሺሕ የአካል መጉደል ያጋጠማቸው ታጣቂዎች፤ በሕወሓት የሰው ኃይል አሥተዳደር ኃላፊ ኮለኔል ነጋሽ ዳኘው አማካኝነት ሰርተፍኬት እና ገንዘብ ተሰጥቷቸው በቅርቡ መሰናበታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ትናንት አርብ ሐምሌ 22/2015 ሰላማዊ ሰልፍ ያካሄዱ ከስድስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች “እኛም አካላችንን ያጣነው ለተመሳሳይ ዓላማ ተሰልፈን የክልሉ መንግሥት ባቀረበልን የዝመቱ ጥሪ ነው፡፡ ለ50 ሺሕዎቹ የተሰጠው ክብርና የተደረገው ድጋፍ ለእኛም ሊደረግ ይገባል፡፡” በማለት መሆኑን ጊደና መድኅን አስረድተዋል፡፡ሰልፍ ከወጡት በተጨማሪ ከቤት መውጣት የማይችሉ በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ወጣቶች በቤተሰቦቻቸው ላይ ሸክም ሆነው ይገኛሉ ያሉት የፓርቲው አደራጅ፤ “እነሱን ዞር ብሎ ያያቸው የለም፡፡” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

“የሕወሓት ሹማምንት ልጆቻውን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ካናዳ እንዲሁም ሌሎች አገራት እያኖሩና እያስተማሩ፤ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የትግራይ የድሃ ልጆችና ወጣቶችን ለሥልጣናቸው ሲሉ እንዲሞቱ እና አካላቸው እንዲጎድል አድረገዋል፡፡” ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም “የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ዓለም ባንክ፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከመሳሰሉ ምግባረ ሰናይ ተቋመት ጋር በመሆን እንዲሁም ከተሃድሶ ኮሚሽን ጋር በመተባበር፤ እነዚህን ወጣቶች በዘላቂነት ይደግፋሉ ብለን ተስፋ እናገርጋለን፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።

በተመሳሳይ ከወራት በፊት በመቀሌ ከተማ አቅራቢያ ሰልፍ የወጡ በጦርነቱ ወቅት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችም በአስለቃሽ ጭስ እንዲበተኑ መደረጋቸው ይታወሳል።

በጉዳዩ ላይ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት አዲ ማለዳ የአስተዳደሩ አመራር ወደ ሆኑት ክንደያ ገ/ሕይወት (ፕ/ር) የእጅ ስልካቸው ብትደውልም ሆነ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ብትልክም ማግኘት ባለመቻሉ ሳይሳካ ቀርቷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለኹለት ዓመት የዘለቀው አስከፊ ጦርነት በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት እና የአካል ጉዳት የዳረገ ሲሆን፤ በአፋር አማራና ትግራይ ክልሎች መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመትም አስከትሏል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here