ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በሳኡዲ ዐረቢያ እስር ቤት ውስጥ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በሳኡዲ እስር ቤቶች የነበሩ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ወደ አገሪቷ የተለያዩ እስር ቤቶች በገፍ ሲጋዙ የነበሩት ኢትዮጵያውያን አሁንም ድረስ በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው የሚናገሩት የመረጃ ምንጮች፤ እስረኞቹ እንደ ጂዛን፣ ሪያድ፣ ጂዳ፣ ጠሪክ ዓልከርጂ፣ ሹሜይሲ፣ ጣሂር እንዲሁም ሃይር በመሳሰሉ የአገሪቱ እስር ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህም አረጋውያን፣ ነፍሰጡር ሴቶች፣ ሕጻናት እንዲሁም ታማሚዎችም እንደሚገኙ አስረድተዋል።
በእስር ቤቶቹ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚደርስባቸው አሳዛኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሕመምና፣ በረሃብ እንዲሁም ራሳቸውን በማጥፋት ሕይወታቸው እያለፈ ይገኛል ሲሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል። በዚህም ረገድ በየሳምንቱ አራት እና አምስት ሰዎች ሕይወታቸው እንደሚያልፍ አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የአየር ንብረት ሞቃታማ መሆን እና በአንድ ክፍል ውስጥ በርካታ ሰዎች ከመታሰራቸው ጋር በተያያዘ እስረኞቹ በተላላፊ በሽታ እንዲጠቁ ሆኗል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በርካቶች በአዕምሮ መታወክ እና በጭንቀት መታመማቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ እስረኞቹ የሚለብሱት ልብስ ከላያቸው ላይ በማለቁ ፊስታል ለብሰው እንደሚተኙም ተነግሯል፡፡
በሳውዲ አረቢያ በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ኢትዮያውያን ቁጥራቸው ከ100 ሺሕ በላይ ነው ይባል እንጂ፤ መንግሥት ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሚል በኹለት ዙር እስረኞችን ወደ አገር መመለሱ የሚታወቅ ሲሆን በዚህም እስካሁን በኹለት ዙሮች ከ132 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር መመለሳችውን አዲስ ማለዳ ከሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሦስተኛው ዙር በቅርቡ እንደሚጀመር የተገለጸ ሲሆን፤ የገቡትን ስደተኞችም አብዛኞቹን ወደ ትውልድ ሥፍራቸው የመሸኝት ሥራ ተሰርቷል ሲል ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
ይሁን እንጂ የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚጠቅሱት፤ በአሁኑ ወቅት በተለይም ከፈረንጆች 2021 አጋማሽ ወዲህ እስረኞቹ ጠያቂ በማጣታቸው እንዲሁም ምንም ዓይነት ድጋፍ ባለማግኘታቸው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አሁን ላይ የሳኡዲ መንግሥት በእስረኞቹ ላይ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የዓለም አቀፉን የስደተኞች መብት አያያዝ ሙሉ ለሙሉ የጣሰ መሆኑ እንዲሁም፤ ለሰብዓዊ መብት የሚታገሉ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች እና ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም በተደጋጋሚ ለአገሪቱ መንግሥት ጥሪ ቢያቀርብም እስካሁን የተገኘ መፍትሄ አለመኖሩ ነው የተገለጸው።፡
ጉዳዩን በሚመለከት በአንድ ሰሞን የነበረው የሚዲያ ዘመቻ እንዲሁም እስረኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ለዓለም ለማሳወቅ የነበው ጥረት መልካም የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመዘንጋቱ ችግሩ ይበልጥ መባባሱ ተጠቁሟል።
በመሆኑም የሰብዓዊ መብት እና የስደተኞች ተቋም፣ በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚሰሩ ተቋማት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግሥት አካላት በአገሪቱ መንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር እስረኞቹን መታደግ እንደሚገባ ነው ምንጮች የሚናገሩት።
አዲስ ማለድ በጉዳዩ ዙሪያ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።



