በትግራይ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተዛውረው የተመረቁ ተማሪዎች መመረቂያ ዲግሪያቸው እንዳልተሰጣቸው ገለጹ

0
761

እሁድ ሐምሌ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ከአክሱም እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው በዘንድሮው ዓመት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የመመረቂያ የምስክር ወረቀት (ቴምፖ) ሳይሰጣቸው ከግቢው እንዲወጡ መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹ “የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 13/2015 ተማሪዎቹን አስመርቆ የመመረቂያ ወረቀት በመስጠት የሸኘ ቢሆንም፤ ከአክሱምና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለመጣን ተማሪዎች ግን “እንድናስተምር እንጂ ቴምፖ እንድንሰጥ የሚያስገድደን አካል የለም።” የሚል ምላሽ መስጠቱ ትልቅ ቅሬታ አሳድሮብናል።” ሲሉ ተናግረዋል።

የመመረቂያ ምስክር ወረቀት ያልተሰጣቸው ተማሪዎች የታሪክ፣ የቪዢዋል አርት፣ የፊዚክስ እንዲሁም የሒሳብ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎም በየቦታው ተዟዙረን ሥራ መፈለግም ሆነ በሚወጡ የቅጥር ማስታወቂያዎች ማመልከት አልቻልንም ብለዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሬጅስተራር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኃላፊ ዶክተር ብሩክ ወልደማሪያም፤ “ተማሪዎቹ ቴምፖ ያልተሰጣቸው፤ በፊት ከነበሩበት ዩኒቨርሲቲዎች ያላቸው መረጃ ሰላልተላከልን ነው።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የተማሪዎቹ መረጃ እንዲላክልን ለአክሱም እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የበላይ አካላት በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን አልተላከልንም ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

ኃላፊው አክለውም፤ ተማሪዎቹ የትምህርት ወጭ (ኮስት ሸሪንግ) መረጃቸው እና የሦስት መንፈቀ ትምህርት ውጤታቸው በፊት ከነበሩበት ዩኒቨርሲቲ ካልተላከ፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ተምረው ባጠናቀቁት የትምህርት ውጤት ብቻ የመመረቂያ የምስክር ወረቀት መስራት አይችልም ነው ያሉት።

በመሆኑም “የትምህርት ወጪ መረጃቸው እና የሦሰት መንፈቀ ትምህርት ውጤታቸው ከአክሱም እንዲሁም መቀሌ ዩንቨርሲቲዎች ሲላክልን ለተማሪዎቹ የመመረቂያ የምስክር ወረቀት ሰርተን የምንሰጥ ይሆናል።” ሲሉ ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here