በሸዋሮቢት ከተማ የጸጥታ ኃይሎች የቤት ለቤት ፍተሻ እና ወከባ እየፈጸሙ ነው ተባለ

የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ኹለት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል

0
1191

እሁድ ሐምሌ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በሸዋሮቢት ከተማ እና አካባቢው የመከላከያ ሠራዊት አባላት የቤት ለቤት ፍተሻ እንደሚያደርጉ እና በነዋሪዎች ላይ ወከባ እየፈጸሙ ነው ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ አክለውም፤ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከተማው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን ጨምሮ በነዋሪዎች ቤት በመግባት “ፋኖ ናችሁ፣ የፋኖ ፎቶ በቤታቸሁ ለጥፋችሗል” በሚል ድብደባ እና ወከባ እያካሄዱ ነው ብለዋል፡፡

ድርጊቱ የተጀመረው ከሐሙስ ሐምሌ 20/2015 መሆኑን በመጠቆም፤ “ጸጉር አሳድገሃል” እንዲሁም “በእጅ ስልክ ቀረርቶና የፋኖ ምስል ጭነሃል” በሚል ሰላማዊ ሰዎችን ላይ ድብደባ እንደሚፈጽሙ ተመላክቷል።

በዚህም አርብ ሐምሌ 21/2015 የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ አንድ ሰው በጥይት እንዲሁም አንድ በዱላ ተደበደቦ ኹለት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት አባላት በከተማዋ በነዋሪዎች ቤት በመግባት የሚያደርጉትን ድብደባ ተከትሎም አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ቤታቸውን ዘግተው ወደ ደብረብርሃን እየሸሹ መሆኑ ነው የተጠቀሰው።

በከተማዋ ባለው የጸጥታ ችግር በተለይ ሰፊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት የባጃጅ አሽከርካሪዎችም በሚደርስባቸው ወከባ ሥራ ማቆማቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ ባንኮችና የገበያ አዳራሾችም ዝግ መሆናቸው ተጠቁሟል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት፤ የቢሮ ስልክ በተደጋጋሚ ብትደውልም ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለው ውጊያ በተለይም ከሰሞኑ በሸዋሮቢት እና አካባቢው እንዲሁም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደንቢያ ወረዳ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን ተከትሎ በርከት ያሉ ንጹሃን መሞታቸው ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here