ኢትዮጵያዊያን ባለሃብቶች መሬታቸውን ከሱዳን ወታደሮች እየገዙ መሆኑ ተገለጸ

0
1004

ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ ዙሪያ የሱዳን ወታደሮች ጓንግ (አልፋሽጋ) ተብሎ የሚጠራውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት አሁንም ድረስ መቆጣጠራቸውን ተከትሎ፤ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች የራሳቸው የነበረውን የእርሻ መሬት ከሱዳን ወታደሮች ገዝተው እያረሱ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡

በአካባቢው የነበሩ አቅም ያላቸው ባለሃበቶች መሬቱን ከሱዳን ወታደሮቹ መልሰው በመግዛት እያረሱ ነው የተባለ ሲሆን፤ አቅም የሌላቸው ደግሞ ከአካባቢው መፈናቀላቸው ተነግሯል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ የግጭት እና የኃይማኖትና ዕምነት ጉዳዮች የሥራ ሂደት ኃላፊ ዮናስ ጋዲሳ፤ የሱዳን ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ከገቡ ከ2013 ጀምሮ እስከ አሁን ድርስ አካባቢው በቁጥጥራቸው ሥር መሆኑን ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ተቆጣጥረው የሚገኙት የሱዳን ወታደሮች በሜካናይዝድ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ መሆናቸውን በመግለጽ፤ “በፌደራል መንግሥቱ በኩል “ይህን ጉዳይ እኛ እንጨርሳለን እናንተ እንዳትደረሱባቸው” በመባሉ ወታደሮቹን ከአካባቢው ለማስለቀቅ ሙከራ አላደረግንም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።

የሰሜኑ ጦርነት ሊጀመር አካባቢ የሱዳን ወታደሮች አካባቢውን በኃይል በመቆጣጠር፣ የኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችን ካምፕ በማቃጠልና ንብረታቸውን በማውደም ከ230 በላይ ባለሃብቶች ከአካባቢው እንዲፈናቀሉ ማደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

የሱዳን ወታደሮች አሁንም ድረስ እስከ ስምንት ኪሎ ሜትር ዘልቀው በመግባት በመተማ እና ቋራ አካባቢዎች የሚገኙ አውደራፊ (ምድረ ገነት)፣ ፖሊ፣ ሰላም በር እንዲሁም በምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አርባጅራ የተባሉ ቦታዎችን ተቆጣጥረው እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።

ወታደሮቹ በተጨማሪም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚያሻግር ድልድይ መገንባታቸውን እንዲሁም የጦር ኃይል በማደራጀት በተቆጣጠሩት አካባቢ መሰረተ ልማቶችን እያስፋፉ እና ሰሊጥ እያመረቱ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የፌደራል መንግሥቱ “ጉዳዩን በራሴ መንገድ ምላሽ እሰጠዋለሁ” ቢልም፣ እስካሁን መፍትሔ አልተገኘም ነው የተባለው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here