ማክሰኞ ሐምሌ 25 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ መውጫ እና መግቢያ በሮች ላይ በሚገኙ ፍተሻ ጣቢያዎች በጸጥታ ኃይሎች በሚጠየቁት ገንዘብ መማረራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከባድ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ውስጥ የሚንቀሳቀሱበት እና ወደ አዲስ አበባ የሚገቡበት የሰዓት ገደብ መኖሩን ተከተሎ፤ በልዩ ሁኔታ የመንቀሳቀሻ ፈቃድ ያላቸው ተሽከርካሪዎችን የኬላ ጠባቂ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በማስቆም አሽከርካሪዎችን እጅ መንሻ እንደሚጠይቁ አዲስ ማለዳ ታዝባለች፡፡
በጎጃም በር በኩል ወደ አዲስ አበባ ጥሬ ወተት የሚያጓጉዙ አሽከርካሪ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ ወተት በፍጥነት ወደ ፋብሪካ ካልደረሰ ቶሎ ስለሚበላሽና ከጥቅም ውጭ ስለሚሆን በማንኛውም ሰዓት ለመንቀሳቀስ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ፈቃድ ማውጣታቸውን አውስተው፤ “ሆኖም ሕጋዊ ፈቃድ ይዤ ብንቀሳቀስም በተለይ እንጦጦ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ለትራፊክ ፖሊሶች እና ለጸጥታ አካላት ገንዘብ ሳልሰጥ ማለፍ አልችልም፡፡” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
የፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ አሽከርካሪ በበኩላቸው በአዳማ መውጫ በሚገኘው ገላን ፍተሻ ጣቢያ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት እንደሚፈጸም በመጠቆም፤ “ይህ ዓይነቱ ሕገ ወጥነት ባስቸኳይ እንዲቆም የሚመለከተው አካል ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል፡፡” ሲሉ ጠይቀዋል።
አክለውም፤ ሕጉን ተላልፈው የተገኙ አሽከርካሪዎች ሕጋዊ ቅጣቱ 1 ሺሕ ብር ሆኖ ሳለ፤ ለትራፊክ ፖሊሶች እና በቦታው ላሉ ሌሎች የጸጥታ አካላት 500 ብር ከከፈሉ እንደሚያሳልፏቸው ጥቆማቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ ድርጊት ዕለት ከዕለት ከመደጋገሙ የተነሳ ሕጋዊ እየመሰለ ነው ያሉት አሽከርካሪዎቹ፤ “ሰርተን ለእነርሱ ነው የምናስረክበው” ሲሉም ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ መውጫ ሰበታ የፍተሻ ጣቢያ፣ በአምቦ መውጫ አንፎ ፍተሻ ጣቢያ እንዲሁም በደብረ ብርሃን መውጫ ለገጣፎ ፍተሻ ጣቢያ ተመሳሳይ ሕገ ወጥ ተግባራት በስፋት እንደሚፈጸምም አዲስ ማለዳ ከአሽከርካሪዎች ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ለመቆጣጠር እና መጨናነቅ እንዳይኖር በሚል ከባድ ተሸከርካሪዎች በተፈቀደላቸው ሰዓት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ አስገዳጅ ሕግ በማውጣት ላለፉት ኹለት ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም አንድ ከባድ የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪ ከረፋዱ አራት ሰዓት በፊትም ሆነ ከቀኑ አስር ሰዓት በኋላ በከተማዋ መንቀሳቀስ አይችልም።
አዲስ ማለዳ አሽከርካሪዎች ባቀረቡት ቅሬታ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ለአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የሥራ አመራሮች የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብትደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።



