በመዲናዋ የኮንዶም እጥረት መኖሩ ተገለጸ

ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ የኮንዶም እጥረት በመኖሩ በተለይ የመድኃኒት ቤቶች በጥቁር ገበያ እየገዙ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከተለያዩ መድሃኒት መሸጫ ሱቆች ባገኘችው መረጃ ተረድታለች።

መድኃኒት ቤቶቹ በፊት ከሚረከቡት ዲኬቲ ኢትዮጵያ የሚፈልጉትን ያህል ኮንዶም ማግኘት ባለመቻላቸው ምክንያት፤ ከዲኬቲ ኢትዮጵያ ገዝተው ካከማቹ ሻጮች እየገዙ እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት።

በዲኬቲ ኢትዮጵያ በ768 ብር የሚሸጥ አንዱ እሽግ ህይወት ትረስት ኮንዶም፤ ከጥቁር ገበያ በ864 ብር እንደሚሸጥም ተመላክቷል።

እንዲሁም ከዲኬቲ በ1 ሺሕ 56 ብር የሚገዛው ሰንሴሽን ኮንዶም፤ በጥቁር ገበያ በ1 ሺሕ 200 ብር እንደሚገዛ ነው የተገለጸው።

በጤና ሚኒስቴር በኩል መሸታ ቤቶችና ፔንሲዮኖች ኮንዶም የማስቀመጥ ግዴታ የተጣለባቸው በመሆኑ፣ በውድ ዋጋ እንደሚገዙም ተመላክቷል።

በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ የተወሰኑ የመድኃኒት ቤት ባለቤቶች ሰንሴሽን ኮንዶም ከጠፋ መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህ ወቅትም “ሴንሴሽንን ጨምሮ ሕይወት ትረስት ኮንዶም ለማግኘት ዲኬቲ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም “ሳምንት ይገባሉ” ከማለት በስተቀር እስከአሁን ምንም ነገር አልተሰጠንም፡፡” ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም በተለይ በመሸታ ቤቶች የሚሰሩ ሴቶችን ለኤች አይ ቪ፣ የአባላዘር በሽታዎች እና ላልተፈለገ እርግዝና ተጋላጭ አድርጓቸዋል ነው የተባለው።

ከዚህ ቀደም በወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት፣ ቀበሌዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች ኮንዶም ይቀመጥ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ባለው እጥረትና የዋጋ መወደድ ምክንያት ይህን ማድረግ አለመቻሉን መረዳት ተችሏል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዲኬቲ ኢትዮጵያ የስራ ኃላፊ ሰንሴሽን ኮንዶም አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ህይወት ትረስት ኮንዶም ግን በአንጻራዊነት በተሻለ መጠን መኖሩን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ከጤና ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙኩራ ብታደርገም፤ ጥያቄው የቀረበላቸው የሥራ ኃላፊዎች “እኔን አይመለከትም” እና “ዛሬ አይመቸኝም” በማለታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮ ባወጣው ሪፖርት፤ በመዲናዋ ከ25 ሺሕ በላይ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች መኖራቸው እና በአሁኑ ወቅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት 3 ነጥብ 36 በመቶኛ ላይ መድረሱ አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here