ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ ስልሳ ሦስት ሰዎች በሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ

0
1197

ረቡዕ ሐምሌ 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ልዩ ሥሙ ቱሉ ሚልኪ በተባለ አካባቢ ሰኞ ሐምሌ 24/2015 በሸኔ ታጣቂ ቡድን ስልሳ ሦስት ሰዎች ታፍነው መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የደጀን ከተማ ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አንዳርጌ ዘውዴ፤ ድርጊቱ የተፈጸመው 65 ሰዎችን አሳፍሮ ከባህር ዳር ከተማ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት እገታውን የፈጸሙት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ መሆኑን እንዲሁም አቅመ ደካማ ከሆኑ አንዲት ባልቴት እና አንድ ሽማግሌ በስተቀር ሹፌሩን እና ረዳቱን ጨምሮ በአጠቃላይ 63 ሰዎችን አግተው መውሰዳቸውን በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የደጀን ከተማ ሰላም እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አክለውም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሚጓዙ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ መሰል ድጊቶች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ለአብነትም ባለፈው ሰኔ 10/2015 በገርበ ጉራቻ አካባቢ ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ከ50 በላይ አሽከርካሪዎችና መንገደኞች በሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸውን አስታውሰው፤ የመክፈል አቅም ያላቸውን ሰዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው መለቀቃቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና የጸጥታ አካላት የተጓዦችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ እና በክልሉ የሕግን የበላይነት እንዲያስከብሩ ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢው የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ በቅርብ ርቀት መኖሩ ቢገለጽም፤ እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች በጠራራ ፀሐይ ሲፈጸሙ የሠራዊቱ አባላት ምንም ዓይነት እርምጃ መውሰድ አለመቻላቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ ቅሬታን ፈጥሯል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ንጹሃንን በማገት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዝብ መጠየቅ የተለመደ ተግባር እየሆነ መምጣቱ ይታወቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here