ሐሙስ ሐምሌ 27 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአልሸባብ የሽብር ቡድን ማክሰኞ ዕለት በኬንያ መወምበኒ በተባለ ሥፍራ በፈጸመው ጥቃት አንድ ሰው መገደሉ እና ስድስት ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ በአካባቢው ባለ ደን ውስጥ ሆኖ በበርካታ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ማድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ የመንግሥት ባለስልጣናት የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት ከመግለጽ ተቆጥበዋል ነው የተባለው፡፡
በአካባቢው የአሳ እርባታ መኖሩ ተከትሎ የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ በሠራተኞች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸው እና ማክሰኞ ጠዋት ከተፈጸመው ጥቃት በሥፍራው ያሉ ልዩ ኃይሎች እንዳዳኗቸው ዘኢስት አፍሪካ ዘግቧል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የአገር ውስጥ ካቢኔ ዋና ፀሀፊያቸው ሊሙ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን አሳ እርባታ በጎበኙ ከስድስት ቀናት በኋላ ነውም ተብሏል፡፡
የአልሸባብ አማፂ ቡድን በአካባቢው ጥቃት ሲያደርስ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ የተነገረ ሲሆን፤ በትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት እንዲሁም በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ላይም ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚያደርስ ነው የተጠቆመው።
የአልሸባብ የሽብር ቡድን መሰረቱን በሶማሊያ አድርጎ በጎረቤት አገራት ጭምር የሽብር ጥቃት የሚያደርስ ሲሆን፤ ከወራት በፊትም በኢትዮጵያ ድንበር ተመሳሳይ ጥቃት ለመሰንዘር ሙኩራ ማድረጉ ይታወሳል።



