አርብ ሐምሌ 28 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደቡብ ክልል በጉራጌ ዞን የሶዶ ወረዳ ዋና መቀመጫ በሆነችው ቡኢ ከተማ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው እና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚል በአሸባሪነት የተፈረጀው ኃይል፤ በከተማው በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የተፈጸሙት በረቡዕ ሐምሌ 26/2015 ሌሊት አምስት ሰዓት ገደማ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ ጥቃቱ በፖሊስ ጣቢያው የታሰሩ ከ30 በላይ የሽብር ቡድኑን አባላት ለማስፈታት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የታጣቂ ቡድኑ አባላት ወደ ከተማው የገቡት በሞተር ሳይክልና በባጃጅ ተሸከርካሪዎች መሆኑን ጠቅሰውም፤ ከፖሊስ ጣቢያው ጠባቂ ፖሊሶች ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም በተደረገው የተኩስ ልውውጥ በትንሹ ኹለት የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን በማንሳት፤ የታሰሩትን የሸኔ አባላትን ለማስለቀቅ የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱንና ጥቃት ካደረሱት የታጣቂ ቡድኑ አባላት የተያዘ አለመኖሩን አክለዋል።
የሸኔ ታጣቂዎች በዞኑ በተለይም በሶዶ ወረዳ ተደጋጋሚ ጥቃት እንደሚፈጽሙ የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ “በአካባቢው በቂ የመንግሥት የጸጥታ አካላት ባለመኖራቸውም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን፡፡” ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ጠጄ መሐመድ በጉዳዩ ዙሪያ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፤ “ሌላ ቦታ በመሆኔ መረጃው አልደረሰኝም፤ መረጃው እንደደረሰኝ አሳወቃችዋለሁ፡፡” ብለዋል፡፡
ሆኖም ኃላፊው ዘገባው እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፤ በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ ባለመኖሩ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።




Addis maleda is always the best for me from bunch of others