ቅዳሜ ሐምሌ 29 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በዋግኽምራ ዞን ዛታ ወረዳ የመከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ፤ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 የሕወሓት እና የአገው ሸንጎ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው እንደነበር የዛታ ወረዳ አስተዳዳር ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የዛታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ካሳሁን መኮነን፤ “ሐሙስ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በዛታ ወረዳ የሚገኙ መከላከያ ሠራዊት ለግዳጅ ወደ ሌላ አካባቢ በወጡበት ቅጽበት፤ የሕወሓት እና የአገው ሸንጎ ታጣቂዎች በወረዳው ነዋሪ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃት የሰነዘሩት ማይ ልሃም፣ ዛንሲባላ እና ጭልሉ በተባሉ ቦታዎች በሦስት አቅጣጫ መሆኑን እና የዛታ ወረዳን ለመቆጣጠር ታስቦ የተሰነዘረ ጥቃት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አስተዳዳሪው፤ በዛታ ወረዳ ሥር የሚገኙ ዛራ እና ዲንቃ የተባሉ ቀበሌዎች አሁንም ድረስ በአገው ሸንጎ እና በሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ሐሙስ ካደረሱት ጥቃት በኋላ በያዟቸው ኹለት ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን “የሚበላ ምግብ ካላመጣቸሁ” በሚል ድብደባ እያካሄዱ ነው ሲሉ አክለዋል።
የአላማጣ ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ እያሱ በበኩላቸው፤ “በአካባቢው የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ለግዳጅ በሚል ከዛታ ከተማ መውጣቱን ተከትሎ አካባቢውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ የሕወሓት አመራሮችን ጨምሮ የሕወሓትና የአገው ሸንጎ ታጣቂዎች ጥቃት ፈጽመዋል።” ብለዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም፤ በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች እየተደረገ ያለውን የተኩስ ልውውጥ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም፤ የዛታ ወረዳን ለመቆጣጠር በብሬን፣ ስናይፐር እና በሌሎች ከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥረት አድርገው ነበር ሲሉም ተደምጠዋል።
በዛታ እና አካባቢው የሚገኙ የሚሊሻ አባላት ታጣቂዎቹ ለፈጸሙት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ በመስጠት ከአካባቢው እንዲወጡ የተደረጉ ቢሆንም፤ መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ባለመመለሱ በቀጣይም ጥቃት ሊያደረሱ እንደሚችሉ ነው የተጠቀሰው።
በአማራ እና በትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተለይም የይግባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች ይስተዋላሉ።



