በምስራቅ ወለጋ ዞን በመከላከያ ሠራዊትና በሼኔ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ተኩስ መኖሩ ተገለጸ

0
1046

ቅዳሜ ሐምሌ 29 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች በመከላከያ ሠራዊት እና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መኖሩን አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች ሰምታለች።

ኹለቱ ኃይሎች በአካባቢው ከዚህ ቀደምም ውጊያ ሲያካሂዱ ነበር የተባለ ሲሆን፤ በተለይ ከባለፈው ከዕሮብ ሐምሌ 26/2015 ጀምሮ ከፍተኛ ውጊያ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡

በተለይም በጊዳ አያና ወረዳ ጢቃ ጃንግር ከተማ ዕሮብ ሐምሌ 26/2015 ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ድረስ ከፍተኛ የሆነ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ ከኹለቱም ኃይሎች በርካታ ሰዎች ሳይሞቱ እና ሳይቆስሉ እንዳልቀረ ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

በኪረሙ ወረዳ ኪረሙ ከተማ በተመሳሳይ ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ ይህ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት ወቅት ጭምር ውጊያ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውንም አክለዋል።

ነዋሪዎቹ በአካባቢው የሚደረጉ ተደጋጋሚ ግጭቶችን በመሸሽ በየጊዜው እንደሚፈናቀሉ እና ሰሞኑን በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው ውጊያ አሁንም በብዛት ወደ ሻምቡ እና ነቀምት ከተሞች እንዲሁም ወደ ተለያዩ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች እየሄዱ መሆኑ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም በዞኑ በአንገር ጉትን እና አቤ ደንጎሮ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ትልቅ የደህንነት ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች ስርዓት አልበኝነት ከልክ በላይ ሰፍኗል የተባለ ሲሆን፤ ያለምክንያት ሰዎችን ወደ እስር ቤቶች በጅምላ ማጋዝ፣ ከታሰሩ በኋላም ለፍርድ አለማቅረብ፣ በየኬላው የሚደረግ ዝፍሪያ እና የመሳሰሉት ሕገወጥ ተግባራት መበራከታቸውን ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ አካባቢውን ለቆ ለመውጣት የማይቻል መሆኑን ጠቁመው፤ “ጥቃት ሊፈጸምብን ይችላል በሚል ሰቀቀን ውስጥ እንገኛለን።” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ከምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ለማግኘት ጥረት ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here