በደብረ ብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ አለመቻሉ ተገለጸ

ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች በወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ እየቀረበላቸው አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ለተፈናቃዮች ተብሎ የመጣ የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁስ ቢኖርም፤ በከተማዋ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ባለው የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ለተፈናቃዮች ማድረስ አለመቻሉን ነው የጠቀሱት።

ተፈናቃዮች ክረምት በመሆኑ በቂ የእርዳታ አቅርቦት አለመኖሩን የገለጹ ሲሆን፤ በሳምንት 10 እና 15 ኩንታል እህል እንደሚያገኙ፣ አንዳንዴም ለኹለትና ሦስት ሳምንት ምንም ዓይነት እርዳታ የማይቀርብበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።

በከተማዋ በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉትን ሳይጨምር ከ23 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሦስት መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ የተባለ ሲሆን፤ ይህ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት ወቅት ከአራት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በሚኖሩበት ባቄሎ ካምፕ አጠገብ የከባድ የመሳሪያ ተኩስ መኖሩ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በሌሎች መጠለያ ጣቢያዎችም ተፈናቃዮች ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በከተማዋ ያለው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ለተፈናቃዮች ካለው ረሃብ ጋር “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የሰሜን ሸዋ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ደረጀ ይንገሱ፤ በወይንሽት እና ቻይና መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ስላለው የጸጥታ ችግር እና የእርዳታ አቅርቦት ሁኔታ ማወቅ አለመቻላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ቡድን መሪው አክለውም ከባድ ተኩስ ያለው በደሴ መውጫ ማረሚያ ቤቱ አካባቢ መሆኑን ገልጸው፤ አራት ሺሕ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ባሉት ባቄሎ ካምፕ የበቆሎ ዱቄት እየተከፋፈለ እንደሚገኝና ሰብዓዊ እርዳታውን እንደቀጠለ መሆኑን አመላክተዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከኦሮሚያ ክልል፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከ70 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸው ይጠቀሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here