ኦነግ ብልፅግና መራሹ መንግሥት አገሪቷን ወዳልተፈለገ አዘቅት እየከተታት ነው አለ

0
1436

ማክሰኞ ነሐሴ 2 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ብልፅግና መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቷን ወደ ያልተፈለገ አዘቅት እየከተታት ነው ብሏል።

በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ድረስ በመላ የአገሪቱ ክፍል ሰላም እና መረጋጋት ከጠፋ ዜጎችም በሰላም ወጥተው መግባት ብርቅ ከሆነባቸው ሰንብተዋል ነው ያለው።

በዚህም ምክንያት በዚህ አራት ዓመት ብቻ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች አይተኬ ሕይወታቸው ማጣታቸውን፣ አካላቸው መጉደሉንና በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የአገርና የግለሰብ ንብረት መውደሙን ጠቅሶ፤ “ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ቀርቶ ሰው በመሆናቸው ብቻ ያገኙት ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ በየትኛው ዓለም ያልተደረገ ድርጊት በዜጎች ላይ ተፈጽሟል፡፡” ሲል አክሏል።

“ለዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ አገሪቷን እየመራ ያለው እና ሥልጣን የጨበጠው መንግሥት ነው” ያለው ኦነግ፤ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ኃይል ለመጠቀም መሞከር አሁንም ለከፋ ውድቀት የሚዳርግ መሆኑ ጠቅሷል።

“የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ወደ አገር ገብቶ ሰላማዊ ትግል ማድረግ ከጀመረበት ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ በአገሪቷ እየሆነ ስላለው ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ዙሪያ አገሪቷን ከሚመራው መንግሥት ጋር ለመወያየት እና ዜጎች ከዚህ በከፋ መልኩ እንዳይጎዱ ለማድረግ በተደጋጋሚ ኹሉን አካታች የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅ ጥሪ ቢያደርግም ጆሮ የሰጠው አካል የለም፡፡” ሲልም ኮንኗል፡፡

“አሁንም መንግሥት አገሪቷ ሰላም እንድትሆን የሚፈለግ ከሆነ፤ ምንጊዜም ቢሆን በተቻለ አቅም ሰላማዊ መንገድን ብቻ መከተል ይኖርበታል” በማለት፤ በየትኛውም የአገሪቱ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በጽኑ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በ“ፋኖ” ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት፤ ከዚህ በበለጠ እልቂት እና ደም መፋሰስ ሳያስከትል እንዲሁም ችግሩ ወደሌሎች ቦታዎች ሳይዛመት በጊዜ መቆጣጠር ያሻል ሲልም አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም አገሪቷ ላጋጠማት ፖለቲካዊ ውድቀት እና ኪሳራ በዚህም ምክንያት የገባችበትን አዘቅት ተመልክቶ ግንባሩ መፍትሄ ሲያፈላልግ እንደቆየ እና በተለያዩ ጊዜያት የመፍትሄ አቅጣቻዎችን ሲጠቁም እንደነበረ በመግለጽ፤ አሁንም ችግሩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ይህንኑ ድርጊት እንደሚገፋበት አስገንዝቧል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here