የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን ወደ አማራ ክልል ያቀኑ መምህራን ወደ መጡበት መመለስ አለመቻላቸውን ተናገሩ

0
578

ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን ወደ ክልሉ ያቀኑ የዩንቨርሲቲ መምህራን ወደ መጡበት አካባቢ መመለስ አለመቻላቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከሐምሌ 25 እስከ 27/2015 ለ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሰጥ በነበረው ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ፈታኝ የነበሩ እና ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህር፤ “ፈተናው በጸጥታ ችግሩ ምክንያት መቋረጡን” ገልጸው፤ ፈታኝ መምህራንም እስካሁን ድረስ መውጫ መንገድ አጥተው በዚያው ዩኒቨርሲቲው በያዘላቸው ሆቴል ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ የምግብ እና የመኝታ አገልግሎት እንዳልተቋረጠባቸው የገለጹት መምህሩ፤ “ነገር ግን ቀጥሎ ምን ሊፈጠር ይችላል” በሚል ስጋት ውስጥ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም፤ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን እና የከባድ መሳሪያ ድምጽ ያለማቋረጥ እንደሚሰማ ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ወደ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ብሔራዊ ፈተና ለመፈተን የሄዱ መምህር፤ “ስለ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስናወራ ነገሮች መስመር እስኪይዙ እና የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ እስኪሆን ባላችሁበት ቆዩ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡

ወደ ደብረማርቆስ ዩንቨርሲቲ በፈታኝነት ተመድበው የሄዱ የዩንቨርሲቲ መምህራንም እስካሁን ወደ መጡበት ቦታ አለመመለሳቸውን መረዳት ተችሏል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ እንዲሁ ካለው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ ራቅ ካለ ሥፍራ ፈተናውን ሊፈተኑ የመጡ ተማሪዎች በዚያው በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች መኝታ ክፍል እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡

የ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዘንድሮ ለኹለተኛ ጊዜ የፈተና ስርቆትን ለመከላከል በሚል በዩኒቨርሲቲዎች የተሰጠ ሲሆን፤ በአማራ ክልል በአገር መከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ የነበረው ፈተና መቋረጡ እንዲሁም አንድ መምህር እና ኹለት ፖሊሶች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

አዲስ ማለዳ ወደ አካባቢያቸው መመለስ ባልቻሉ ፈታኝ መምህራን እና ተፈታኝ ተማሪዎች ጉዳይ ከትምህርት ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገችው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here