ኤርትራዊያን በብሔራዊ አገልግሎት ወቅት ስቃይ እና ጾታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተገለጸ

0
640

ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኤርትራዊያን በግዴታ ብሔራዊ አገልግሎት ወቅት ስቃይ፣ ኢሰብአዊ ወይም አዋራጅ አያያዝ፣ ጾታዊ እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም የግዳጅ ሥራ እና በደል እየደረሰባቸው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

ተቋሙ ከኤርትራዊያን ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፤ የኤርትራ መንግሥት ብሔራዊ አገልግሎቱ የአገልጋዮችን ሰብዓዊ መብት እንዲያረጋግጥ እና ዓለም አቀፍ ደንቦችን እንዲያከብር ከሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች የሚቀርብለትን በርካታ ጥሪዎች ችላ ማለቱን ጠቁሟል።

ከ30 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ነጻ አገር መሆኗን ያወጀችው ኤርትራ፤ ዕልቆ ቢስ የሚባል የግዴታ የሲቪልና የወታደራዊ ብሔራዊ አገልግሎት ወጣቶችን ለስደት የሚዳርግ ዋነኛ ምክንያት መሆኑም ተሰምሮበታል።

የኤርትራ የብሔራዊ አገልግሎት መርሃ ግብር በተለይም በግዳጅ ብሔራዊ ወታደራዊ አገልግሎት ወቅት ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርቶች መኖራቸው ተጠቅሷል።

አገራዊ ልማት ማስፋፊያ በሚመስል መልኩ የተዘረጋው የብሔራዊ አገልግሎት መርሃ ግብር፤ ወጣቶችን ለስደት በመዳረግ የኤርትራ ልማትን እያናጋ ነው ተብሏል።

የኤርትራን መንግሥት በህሊና እንኳን መቃወሚያ አይፈቀድም የተባለ ሲሆን፣ ተቃውሞ የሚያሰሙ አካላት ለዘፈቀደ እስራት፣ ከፍተኛ ቅጣት፣ ለመጥፋት እና መሰቃየት እንደሚጋለጡ ነው የተገለጸው።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኤርትራን በዓለም ላይ እጅግ ጨቋኝ ከሆኑ አገራት አንዷ መሆኗን ይገልጻሉ።

ሉዓላዊት አገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ኤርትራን ያለተቀናቃኝ እየገዙ ያሉት ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአገራቸው ምርጫ እንዲካሄድ፣ ተጠያቂነት እንዲሁም የስልጣን ክፍፍል እንዲኖር ፈቃደኛ አለመሆናቸው ይጠቀሳል።

በዚህም ፕሬዘዳንቱ በተለይ ከአሜሪካ እና ምዕራባውያን አገራት ጋር የረዥም ጊዜ የሻከር ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፤ አገራቸውም የበርካታ ማዕቀቦች ሰለባ ናት።

ሰሞኑ በስፔን በተዘጋጀ የኤርትራውያን ዝግጅት ላይ በፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ደጋፊና ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ኹከት 52 ሰዎች መጎዳታቸው ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here