ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የሚያዋስናትን ድንበርን መዝጋቷን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጣለች።
በአማራ ክልል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው የሚጠሩ ኃይሎች በይፋ ወደ ግጭት ከገቡበት ከሐምሌ 23/2015 ጀምሮ፤ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ መግባትም ሆነ ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን መውጣት መከልከሉ ነው የተገለጸው።
በሱዳን የተቀሰቀሰውን ግጭት ተክትሎ በርካታ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት በመተማ በኩል መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ “ከሱዳን ገላባት በተባለ ቦታ አድርገው ወደ መተማ ወረዳ የሚያስገባውና የሚያስወጣው ድንበር በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በፌደራል ፖሊስ እንዲዘጋ ተደርጓል፡፡” ብለዋል፡፡
ድንበሩ እንዲዘጋ የተደረገው በጎንደር እና አካባቢው በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ መካከል እየተደረገ ያለውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ፤ በስደተኞች ሥም ችግር ፈጣሪዎች እንዳይገቡና እንዳይወጡ እንዲሁም መንግሥት በአማራ ክልል እያካሄደው ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንዳይደናቀፍ ታሰቦ ሳይሆን እንዳልቀረ ጠቁመዋል፡፡
ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ፤ የሱዳን ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ በመተማ ድንበር በኩል ከ60 ሺሕ በላይ ስደተኞች የሱዳንን ቀውስ ሸሽተው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ጠቁመው፤ ከሐምሌ 23/2015 ወዲህ ግን ድንበሩ መዘጋቱንና ስደተኞችም እየገቡ አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ “በአማራ ክልል የተፈጠረውን ቀውስ በመጠቀም ከጎንደር እና አካባቢው በሕገወጥ መንገድ ወደ ሱዳን የሚደረግ የንግድ ዝውውር እየተስፋፋ በመሆኑ ድንበሩ እንዲዘጋ ምክንያት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
አካባቢውንም የኢትዮጵያ የጸጥታ እና የደህንነት የጋራ ግብረሃይል ከመከላከያ ሠራዊት እና ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን እየጠበቀው መሆኑን ነው የገለጹት።
በመተማ እና በሱዳን ድንበር አካባቢዎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጭምር ተሳታፊ የሆኑበት ሕገወጥ ንግድ መስፋፋቱን ተከትሎ፤ ቡና፣ ሳሙና፣ ብስኩት፣ የታሸገ ውሃ፣ ሻይ ቅጠል እንዲሁም ሌሎች ሸቀጣሸቀጦች በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ሱዳን ሲላኩ እንደነበር ከዚህ ቀደም አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።
በጎንደርና አካባቢው በርካታ የሱዳን ስደተኞች መኖራቸውና ትኩረት የሚሰጣቸው አካል ባለመኖሩ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በአካባቢው በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው ውጊያ በተባራሪ ጥይት ሳይሞቱ እንዳልቀሩም ተመላክቷል።



