በሰላም በር ከተማ ባለፈው ሳምንት በመንግሥት አመራሮች የተመራ የረብሻና አመፅ ቅስቀሳ ተደርጎ ነበር ተባለ 

0
899

ሐሙስ ነሐሴ 4 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ከአዲሱ “የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል” አደረጃጀትና ምስረታ ሂደት ጋር ተያይዞ የክልሉ አደረጃጀት “የጋሞ ሕዝብን ጥቅም የሚነካ አደረጃጃት በመሆኑ አንቀበልም” በማለት፤ ሐምሌ 29/2015 በቁጫ ምርጫ ክልል በቁጫ ወረዳና በቁጫ ሰላምበር ከተማ አስተዳደር ውስጥ በመንግሥት አመራሮች የተመራ የረብሻና አመፅ ቅስቀሳ ተደርጎ ነበር ሲል የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁሕዴፓ) አስታወቀ፡፡

ፓርቲው ከአዲሱ ክልል አደረጃጀትና ምስረታ ሂደት ጋር ተያይዞ በቁጫ ምርጫ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ዛሬ ነሐሴ 4/2015 መግለጫ ሰጥቷል፡፡

በመግለጫውም በአካባቢው “በመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተቀስቅሶ ተመርቷል” ባለው አመፅና ረብሻ፤ በርካታ ጥፋቶች መድረሳቸውን ገልጿል፡፡

በዚህም የቁጫ ሕዝብን ከወላይታ ዞን፣ ከጎፋ ዞን እና ከደቡብ ኦሞ ዞን ሕዝብ ጋር የሚያገናኘው ዋና የአስፓልት መንገድ እንደተዘጋና የሕዝብን ነፃ እንቅስቃሴ በመገደብ ወደ ቁጫ ሰላምበር ከተማ ቅዳሜ ገበያ የመጣው ገበያተኛ እንዲበተን መደረጉን፤ የቁጫ ሕዝብ ተወካይ እና ምክር ቤት አባል ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ ገዳሱ ተናግረዋል፡፡

“በአካባቢው የጸጥታ ኃይሎች በገበያተኞች ላይ ወከባ፣ ድብደባና ኃይልን የመጠቀም ሁኔታ ነበር” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ገነነ፤ በረብሻው ያልተሳተፉ የሰላምበር ከተማ ነዋሪዎች፣ የቁጫ ብሔረሰብ አባላት እንዲሁም የፓርቲው አባላትና አመራሮች ንግድ ተቋማት እና መኖሪያ ቤቶች ላይ በተፈጸመ የድንጋይ ውርወራ ውድመት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በረብሻው ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል የአንዱ ሕይወት ማለፉን በማንሳት፤ ሌሎች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ሀብታሙ ሃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ “ረብሻው እጅግ ከፍተኛ ግጭትና ውድመት እንዲሁም ኪሳራ እንዲደርስ ታቅዶ የተፈጸመ ነበር” ብለዋል፡፡ነገር ግን በወቅቱ ከቁጫ ሕዝብ እና ከፓርቲው ለክልሉና ለፌዴራል ጸጥታ እና ተጠሪ ተቋማት በቀረበው ጥቆማ እና አቤቱታ መሰረት የፌዴራል ጸጥታ ኃይል ወደቁጫ ወረዳ እና ቁጫ ሰላምበር ከተማ በአስቸኳይ በመድረስ ሕዝቡን መታደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

“የአመፅ ቅስቀሳ እና ረብሻው በአካባቢው እንዲነሳ የተፈለገው በዋናነት የቁጫ ሕዝብ በሚኖርበት መልክዓ ምድሩ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ከረጅም ዘመናት ጀምሮ “የቁጫ ብሔረሰብ የማንነት ዕውቅና እና የራስ አስተዳደር ዞን መዋቅር ሕገመንግሥታዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተፈጥሯዊ የመብት ጥያቄዎች በተገቢው ኹኔታ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዳያገኝ ለማድረግ ነው” ሲሉም ምክትል ሰብሳቢው አክለዋል፡፡

ፓርቲው በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው አንጻራዊ መረጋጋት መታየቱን የገለጸ ሲሆን፤ የተገኘው አንፃራዊ መረጋጋት ወደ አስተማማኝ ደረጃ እስኪደርስ እና አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምስረታ ተካሂዶ፤ አካባቢው ወደዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እስኪመለስ ድረስ፤ ገለልተኛው የፌዴራል ጸጥታ ኃይል የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት እንዲጠብቅ በመንግሥት በኩል ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም በቁጫ ሕዝብ ፖለቲካዊ መብት እና ተሳትፎ ላይ ሌሎች ኃይሎች እንዲወስኑ ዕድል የሚሰጠው ኢ-ፍትሐዊ አካሄድ በአስቸኳይ እንዲቆም ፓርቲው አሳስቧል፡፡በዚህም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቁጫ ብሔረሰብ ማንነት እና የራስ አስተዳደር የዞን መዋቅር ሕገመንግሥታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን በሕገመንግሥቱ በተቀመጠው አግባብ ፈጣን ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ብሏል፡፡

ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ክልል ምስረታ ሂደት ጋር ተያይዞ ዕኩይ ፍላጎት ያላቸው አካላት በፈጠሩት ረብሻ እና አመፅ ለሰው ሕይወት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑና በረብሻው የተሳተፉ አካላት እንዲሁም፤ የቁጫ ምርጫ ክልል ሕዝብ ተወካዮች ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር እንዳይገናኙ በማድረገ ጥቃት የፈጸሙባቸው አካላት ለሕግ ሊቀረቡ ይገባልም ነው ያለው፡፡

አክሎም የመንግሥት አካላት በመሩት ኹከት የሰው ሕይወት ለጠፋበት የሟች ቤተሰብ እና በብጥብጡ  የአካልና የንብረት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎ፤ ተገቢው ካሣ እንዲከፈል እና የወንጀሉ ፈፃሚዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ፓርቲው በመግለጫው ጠይቋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here