ቅዳሜ ነሐሴ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉተን ከተማ ማንነትን መሰረት ያደረግ ድብደባ፣ የጅምላ እስር እና ዘረፋ እየተፈጸመ መሆኑን ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ጥቃቱ የጀመረው ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 ጠዋት ኹለት ሰዓት ገደማ በከተማው በሚገኝ የአንድ የትምህርት ቤት የጥበቃ ሠራተኛ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ “ከእናንተ ወገን ነው የገደለው” በሚል የማንነት ጥቃት እየደረሰብን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ድብደባው እና የጀምላ እስሩ እንዲሁም የቤት ለቤት ዘረፋው ነሐሴ 04/2015 ረፋድ ጀምሮ የቀጠለ መሆኑንም በመግለጽ፤ “ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉት የመንግሥት የጸጥታ አካላት ልብስ የለበሱ እና የታጠቁ ኃይሎች ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ እየተፈጸመባቸው ባለው ማንነት ተኮር ጥቃት ሳቢያ እየተፈናቀሉ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በክልሉ በተለይም ወለጋ አካባቢዎች ለከተታይ ዓመታት በዘለቀ የጸጥታ ችግር የንጹሃን ሰዎች ሞትና መፈናቀል አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከአካባቢው የመንግሥት አካል ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።




እንዲህ አይነት ችግሮች በተደጋጋሚ ሲከሰቱ ነበር አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ከነቀምት – ጉትን ያለው መስመር ማንነትን መሰረት ያደረገ ግድያና ዝርፊያ ይፈፀምበታል በዋናነት በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ፡፡ጉዳዮ ከሀላፊዎቹ በላይ ሆኖ ሳይሆን ለማስተካከል ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው፡፡