የሕወሓት አመራሮች ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ ወደ ራያ በኃይል ለመግባት ማቀዳቸው ተሰማ

0
1454

ቅዳሜ ነሐሴ 6 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሕወሓት አመራሮች ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 በመሆኒ ከተማ ባደረጉት ሚስጥራዊ ስብሰባ፤ “የራያ አካባቢዎችን ከነሐሴ 16/2015 እስከ መስከረም 01/2016 ባለው ጊዜ በኃይል እንቆጣጠራለን” ማለታቸውን አረጋግጫለሁ ሲል የአላማጣ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የአላማጣ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ሞገስ እያሱ፤ “በራያ አላማጣ የወሰንና የማንነት ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ እንዲያገኝ መታቀዱን ተከትሎ የሕወሓት አመራሮች በመሆኒ ከተማ ባደረጉት ስብሰባ፤ “ሕዝበ ውሳኔውን ማደናቀፍ አለብን” በሚል ከነሐሴ 16/2015 ጀምሮ ውጊያ ለመክፈት ወስነዋል፡፡” ነው ያሉት።

ኃላፊው አክለውም፤ “የመከላከያ ሠራዊት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር እየተደረገ ባለው ውጊያ በመዳከሙ፤ ራያን ከነሐሴ 16/2015 እስከ መስከረም 01/2016 ድረስ እንቆጣጠራለን የሚል ዕቅድ ማውጣታቸውን ከተሰብሳቢዎች መረጃ አግኝተናል፡፡ ብለዋል፡፡

በራያ አላማጣ የሚገኙ ስድስት ወረዳዎች በዋናነት በጀት እንዲለቀቅላቸው የሚጠይቅ በፊርማ የተደገፈ የሕዝብ አቤቱታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስገባታቸውን ተከትሎ፤ የሕወሓት አመራሮች የሕዝበ ወሳኔው ሃሳቡን ሲቃወሙ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

“የሕወሓት አላማ በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ መካከል እየተደረገ ያለውን የተኩስ ልውውጥ እንደአጋጣሚ በመጠቀም የራያ እና አላማጣ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ያለመ ቢሆንም፤ አንድ ቀን ያሰቡትን ድርጊት ሊፈጽሙት ይችላሉ በሚል የአካባቢው ነዋሪ በቂ ዝግጅት አድርጓል” ሲሉም ተደምጠዋል።

የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ ከንቲባ ሃይሉ አበራ ጉዳዩን አስመልክቶ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ምላሽ፤ “የሕወሓት አመራሮች አደረጉት ስለተባለው ስብሰባም ሆነ “ራያን በኃይል እንቆጣጠራለን” ማለታቸውን አልሰማሁም፡፡ እስካሁንም መረጃው አልደረሰኝም” ብለዋል።

ይሁን እንጂ “በሃሳብ ደረጃ ግን ሁልጊዜ የሚወራ ጉዳይ ስላደረጉት እና በኃይል እንገባለን የሚል አማራጭ ስላስቀመጡ አንድ ቀን ሊያደረጉት እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡” ብለዋል፡፡

“የአካባቢው ማህበረሰብ ዝግጁ ስለሆነ አያሰጋንም” ያሉት ኃላፊው፤ ጦርነት ለመጀመር ካሰቡ ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ከሚገኘው ከመከላከያ ሠራዊት ጋርም እንደሚጋጩ እና የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይፈጸም እንቅፋት እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

የወልቃይት እና የራያ አካባቢዎች በትግራይ እና አማራ ክልል ዋነኛ የይገባኛል ጥያቄ የሚቀርብባቸው ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በቅርቡ ፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች በሕዝበ ውሳኔ እልባት ሊያገኙ እንደሚችሉ ጥቆማ መስጠታቸው ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here