ረቡዕ ነሐሴ 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል ዓለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች አስቸካይ ሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማቋረጣቸው ተከትሎ፤ በሦስት ዞኖች ብቻ 1 ሺሕ 411 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የትግራይ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ገብረሕይወት ገ/እግዛብሔር ለድምፂ ወያነ እንደገለጹት፤ በትግራይ ያለው የረሃብ አደጋ አሳሳቢ እና እጅግ አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
ወቅቱ የክረምት ወራት ከመሆኑ ጋር ተያይዞም ብርድና ዝናብ ተጨምሮ ሁኔታው እጅግ አደገኛ እንዲሆን ማድረጉን የገለፁት ዶ/ር ገብረሕይወት፤ ሰብአዊ እርዳታ መቋረጡን ተከትሎ በሦስት ዞኖች ብቻ 1 ሺሕ 411 ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል።
በተለይም በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የመጡት ከ2 ነጥብ 6 ሚልዮን በላይ ተፈናቃዮች እጅግ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ መውደቃቸው በመግለጽ፤ በየቀኑ የበርካታ ተፈናቃዮች ሕይወታቸው እያለፈ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በትግራይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እና የበርካታ ዜጎች ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የረሃብ አደጋ ለመከላከል ሰብአዊ እርዳታ ማቅረብ ያቆሙት ለጋሽ ድርጅቶች ሰብአዊ እርዳታ እንዲጀምሩና የአለም አቀፍ ማህበረሰብም ከፍተኛ ርብርብ እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ላለፉት 5 ወራት አቋርጦት የነበረውን የምግብ እርዳታ ስርጭት፤ የእርዳታው ተጠቃሚዎች በምን መልኩ እንደሚመረጡ ከፍተኛ ቁጥጥር ካደረገ በኋላ በያዝነው ሐምሌ ወር ለመጀመር እቅድ መያዙን ማስታወቁ መዘገቡ ይታወሳል፡፡



