ረቡዕ ነሐሴ 10 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የጋሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር ክልል አደረጃጀት የጋሞ ሕዝብ ፍላጎት ያልወከለና በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን “ማንኛውም ብሔር ብሄረሰብ የራሱን ክልል የመመስረት መብት” ያላከበረ ነው ሲል አደረጃጀቱን እንደማይቀበለው አስታውቋል።
ፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክላስተር ክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ፤ “የጋሞ ሕዝብ በክልል የመደራጀትና ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ-መንግሥታዊ መብቱ ሊከበር ይገባል” ያለ ሲሆን፤ “መንግሥት የጋሞ ሕዝብ ያቀረበው ሕጋዊ የክልልነት ጥያቄ እያፈነ ይገኛል” ሲልም ከሷል፡፡
ፓርቲው “የጋሞ ሕዝብ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ገና ምላሽ ባላገኘበት ወቅት፤ የዞኑ አስተዳደርና ገዢው ፓርቲ ራሳቸው የሚቆጣጠሩት ከዓመታት በፊት የተመረጠና፤ በአዲስ ምርጫ ያልታደሰ የዞን ምክር ቤት ሰብስበው፤ “መንግሥት ያስቀመጠው የአደረጃጀት አቅጣጫ” ባሉት የክላስተር ክልል አደረጃጀት የጋሞ ሕዝብ እንዲካተት በማስወሰን ለሕዝብ፣ ለዴሞክራሲና ለሕገ-መንግሥታዊ አሠራሩ ያላቸውን እንቢተኝነት አሳይተዋል” ሲል ነው የገለጸው፡፡
በአሁኑ ሰዓት “በአዲስ መልክ ይደራጃል” ተብሎ የታሰበለት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክላስተር ክልል፤ በየዞኑ በሚቀርቡ የማዕከልነት እንዲሁም የተሻሉ የክልል ቢሮዎችን ወደየራስ የማምጣት ፍላጎቶች መሐል እንደሚገኝም ፓርቲው ገልጿል፡፡
በተጨማሪም “የማዕከልነትና የቢሮ ድልድሉ እጅግ ኢ-ፍትሐዊነት የታየበትን አፈፃፀም እንዳስቀመጠም ከሚወጡ መረጃዎች መረዳት ችያለሁ” ነው ያለው፡፡
“የጋሞ ሕዝብ የራሱ የሆነውን ያለፈቃዱ አሳልፎ የሚሰጥ ሕዝብ አይደለም፡፡” ያለው ፓርቲው፤ “ይህ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦችም ጋር አብሮነቱን አጠናክሮ በሰላምና በፍቅር የሚኖር የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት ሕዝብ ነው፡፡” ሲልም ገልጿል፡፡
የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) “የሕዝብን ፍላጎት ያላማከለው መንግሥታዊ የክልል አደረጃጀት ነው፡፡” ያለውን አደረጃጀት ከእሳቤው ጀምሮ ሲቃወም መቆቱን በማስታወስ፤ ወደ ተግባር ለማስገባት እየተደረገ ያለውንም ጥድፊያ የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለነሐሴ 04/2015 በአርባ ምንጭ ከተማ ጠርቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡
ይህንንም በአዋጁ መሠረት ለሚመለከታቸው አካላት ማሳወቁን የገለጸው ፓርቲው፤ ነገር ግን የጋሞ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ የሕዝብ ሃሳብን የመግለጽ ኹለንተናዊ ሰብዓዊ መብቱን የሚጠቀምበትን አካሔድ በመደፍጠጥ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይከናወን መከልከሉን ገልጿል፡፡
“ሰላማዊ ሰልፉ በተጠራበት ሐሙስ ነሐሴ 04/2015 እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው የግልና የቡድን መሣሪያዎችን የታጠቀ የወታደር ሠራዊት በአርባ ምንጭ ከተማ በየሰፈሩ ተበትኖ ሕዝቡን ሲያስፈራራና ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፉን እንዳይወጡ ሲያፍን ውሏል” ያለው ፓርቲው፤ በዚህም ከ400 በላይ ዜጎች ለእስርና ለድብደባ ተዳርገው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ60 ሰዓታት በላይ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) “መንግሥት የጋሞን ሕዝብ ክልላዊና አገራዊ መብት፣ ጥቅምና ክብር በሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ያላከበረውን የአዲሱን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምሥረታ ሒደትን ከማጣደፍ ተቆጥቦ፤ የመንግሥት ምሥረታ ሒደቱን እንዲያቆም እና የጋሞን ሕዝብ በዚሁ ጉዳይ ከላይ እስከታች የሚያወያበትን አካታችና አሳታፊ መድረኮች በአስቸኳይ እንዲፈጥር” ጠይቋል፡፡
በተጨማሪም “የዞኑ ምክር ቤት ለኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕጋዊ አሠራሩን ተከትሎ ቅሬታ ያቀረበበት የጋሞ ብሔራዊ ክልል ጥያቄ የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በሚያዘው መንገድ ብቻ ታይቶ አስቸኳይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” ብሏል፡፡
እንዲሁም “ፓርቲው ነሐሴ 04/2015 ለጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ሕገ-ወጥነትን በመከተል የጋሞ ሕዝብ ሀሳቡን በነፃነት የመግለጽ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱን የረገጡት የጋሞ ዞን አስተዳደር እና የጋሞ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ በሕግ እንዲጠየቁና ይንንም መንግሥት ተግባራዊ አድርጎ ለሕዝብ ሊገልጽ ይገባል፡፡” ሲል በመግለጫው አሳስቧል፡፡



