ዳሸን ባንክ እና ማስተር ካርድ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን አለም ዓቀፍ “ቨርቹዋል ካርድ” አስተዋወቁ

0
408

አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ዳሸን ባንክ እና ማስተር ካርድ በጋራ በመተባበር፤ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀሪያ የሆነውን “ቨርቹዋል የቅድመ ክፍያ ካርድ” ትናንት ነሐሴ 11/2015 በሸራተን አዲስ ሆቴል በይፉ አስተዋውቀዋል፡፡

ካርዱ ከተለደው እና በሥም ከሚታተመው የፕላስቲክ ካርድ የተለየ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ደንበኞች ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሆነው ገንዘባቸውን ያለምንም ስጋት መጠቀምና ማንቀሳቀስ የሚችሉበት አማራጭ መሆኑም ተነግሯል። በካርዱ ይፋዊ የማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አስፋው ዓለሙ፤ “ዳሸን ባንክ ይህን በአይነቱ የተለየ ካርድ ማስተዋወቁ፤ ባንኩ ለደንበኞቹ ቀላል፣ ምቹና አስተማማኝ የፋይናስ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል” ብለዋል፡፡

ዳሽን ባንክ ከዚህ ቀደም “የውጪ ምንዛሬ ሂሳብ” ላላቸው ደንበኞቹ ብቻ የሚያገለግል ካርድ በሥራ ላይ ማዋሉን ያስታወሱት አስፋው፤ አዲስ የተዋወቀው “ቨርቹዋል የቅድመ ክፍያ ካርድ” በአጠቃላይ ለአለም ዓቀፍ ተጓዦች ታስቦና ከፍተኛ የደህንነት መጠበቂያ ተደርጎለት በአማራጭነት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ደንበኞች ካርዱን ለመጠቀም አቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የበረራ ቲኬት በመያዝ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉም ብለዋል፡፡ቨርቹዋል የቅድመ ክፍያ ካርዱ ከሌሎች የቅድመ ክፍያ ካርዶች የተለየ አማራጮችን ይዞ መምጣቱንም በመግለጽ፤ ካርዱ ከተሰጠ በሗላ ደንበኞች ለራሳቸው በተዘጋጀ ፓርታል ላይ ገብተው በካርዱ ላይ ያለውን የሚስጥር ቁጥር መቀየር፣ ካርዱ ቢሰረቅ የካርዱን እንቅስቃሴ ማስቆም እንዲሁም የተከናወኑ ግብይቶችን ማረጋገጥ እንደሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም አብራርተዋል።

የማስተርካርድ የምስራቅ አፍሪካ ሥራ አስኪያጅ ሸህርያር አሊ በበኩላቸው፤ ማስተርካርድ ከዳሸን ባንክ ጋር የፈጠረው ጥምረት በኢትዮጵያ እንደ አለም አቀም ካርድ ያሉ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ማህበረሰቡ ይበልጥ የዲጂታል አገልገሎቶችን ተጠቃሚ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ ይፈጥራል ብለዋል፡፡“ከዳሸን ባንክ ጋር በመጣመር የተለያዩ የዲጂታል አገልግሎቶችን ለማቅረብና ይህን መሰል የክፍያ አማራጭ ለንግዱ ማህበረሰቡና ሌሎች ደንበኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻላችን ትልቅ ክብር ይሰማናል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዳሸን ቅድመ ክፍያ ማስተርካርድ ደንበኞች ከኤቲኤም እና ፖስ በተጨማሪ በኢ-ኮሜርስ ክፍያ መክፈል የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ደንበኞች ፕላስቲክ ወይም ቨርቹዋል ካርድ በመውሰድ መጠቀም ይችላሉ ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፕላስቲክ ካርዱ ሥም የታተመበትና ሥም ያልታተመበት የካርድ አይነቶችን የያዘ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ደንበኞች ዳሸን ማስተር ካርድ ላይ የተሞላው የውጪ ምንዛሬ ሲያልቅ እንደገና በመሙላት መጠቀም የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ካርዱን ኤቲኤምና ፖስ ማሽን ላይ በማስገባት ወይም ያለ ንክኪ ገንዘብ ማውጣት ወይም ክፍያ መፈጸም እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡

ፕላስቲክ ካርዱ በሚስጢር ቁጥር የተጠበቀ ሲሆን፤ ቨርቹዋል ካርዱ ደግሞ በአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡ዳሸን ባንክና ማስተርካርድ ከካርዱ በተጨማሪ የንግድ ተቋማት ክፍያቸውን በበይነ መረብ ከየትኛውም የአለም ክፍል መቀበል የሚያስችል የማስተርካርድ የክፍያ መቀበያ ማስተርካርድ ጌትዌይ (MasterCard Payment Gateway System) ሲሆን፤ ይህም ሦስት የካርድ አይነቶችን በመቀበል የተሻለ የአገልግሎት አማራጭ የያዘ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ማስተርካርድ ጌትዌይ ለንግድ ተቋማት ክፍያ ለመቀበል እና ሽያጭ ለማከናወን ለምግባረ ሰናይ ድርጅቶች እርዳታ እና የአባልነት ክፍያ ለመሰብሰብ እና ለሌሎች አገልግሎቶች ዘመናዊ የክፍያ መፈጸሚያ መስመር መሆኑ ተነግሯል፡፡

ማስተር ካርድ በአለማቀፍ ደረጃ በ210 አገራት ውስጥ ክፍያ የሚፈጸም እና ከ1.9 ቢልዮን በላይ ተጠቃሚ ደንበኞች ያሉት ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብይቶችን በማስኬድ፣ ሸማቾችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ ነጋዴዎችን፣ መንግሥታትን እና ንግዶችን በዓለም ዙሪያ በማገናኘት እና ክፍያዎችን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች በማስቻል ይታወቃል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here