አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የክፍለ ጦሩ የሠራዊት አባላት የጥፋት እጁን በመዘርጋት ሠላምን አልቀበልም ያለው የሸኔ ቡድን ላይ እየወሠዱት ያለውን ርምጃ አጠናክረው መቀጣላቸውን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አስታውቋል።
በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሕዝቡን ሠላም መንሳት ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀሰው የሽብር ቡድኑ ሸኔ፤ በሠራዊቱ እና በሕብረተሠቡ የጋራ ትብብር ፍላጎቱን ማምከን እና በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የተገለጸው።
ከሠሞኑም በምዕራብ ሸዋ ዞን ብጥሌ በተባለ ቦታ 20 የሽብር ቡድኑ ሸኔ አባላት ላይ ርምጃ ሲወሠድ 13ቱን በማቁሰል 18 የሸኔ አባላትን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፤ በተጨማሪም ቡድኑ ይጠቀምበት የነበረው የሎጅስቲክስ ቁሳቁሶች በክፍለጦሩ አባላት እጅ መግባቱን በቀጠናው የሚገኘው ክፍለጦር አዛዥ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በምዕራብ ሸዋ ዞን በኢሉ ገላን ወረዳ ረፍሶ ቋሚና በተባለ ቦታ 18 የሸኔ አባላት ሲገደሉ 2 አባላት መማረካቸው ተገልጿል፡፡ ቡድኑ ታጥቆት የነበረ አንድ ብሬን፣ ስድስት ክላሽ፣ ሰባት የብሬን ሰንሰለት፣ 35 የብሬን ጥይት ሰባት የወገብ ትጥቅ እንዲሁም 20 የክላሽ መጋዘን በክፍለ ጦሩ ቁጥጥር ሥር መዋሉን አዛዡ ገልጸዋል።
“መንግሥት በኢትዮጵያ ሠላም ሠፍኖ ሕዝቡ የልማት ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ለሸኔ እና መሠል ዓላማ ላላቸው ሃይሎች የሠላም ጥያቄ ቢያቀርብም ጥያቄውን ወደ ጎን በመተው ከሠላም ይልቅ ጦርነትን ከአንድነት ይልቅ መለያየትን የመረጡ የአብሮነት ጠንቆች ሠላም መርጠው ከድርጊታቸው እስካልተቆጠቡ ድረስ ርምጃዎች የሚቀጥሉ መሆናቸው” መገለጹን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡



