አርብ ነሐሴ 12 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል የተከሰትውን ቀውስ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በምግብ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች ከሚገኙ ነዋሪዎች ባደረገችው ማጣራት አረጋግጣለች።
በክልሉ በተፈጠረው ቀውስ ምክንያት መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ፤ ከአዲስ አበባና የተለያዩ አካባቢዎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን ማስገባት ባለመቻሉ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መስተዋሉ ነው የተገለጸው።
ለአብነትም በክልሉ ጎንደር፣ ባሕርዳር፣ ደሴ፣ ደብረብረሃን እና ደብረማረቆስ ከተሞች ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው ሐምሌ እኩሌታ በፊት ጤፍ በኩንታል ከ8 እስክ 9 ሺሕ ሺሕ ብር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ10 እስከ 11 ሺሕ ብር እየተሸጠ ይገኛል።
እንዲሁም ከ800 እስከ 900 መቶ ብር ሲሸጥ የነበረው አምስት ሊትር የምግብ ዘይት፤ በአሁኑ ወቅት ከ1 ሺሕ 200 እስከ 1 ሺሕ 300 ብር እየተሸጠ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
ከተፈጠረው ክልላዊ ቀውስ በፊት በእነዚህ ከተሞች የዳቦ ዱቄት በኩንታል እስከ 7 ሺሕ 500 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት ከአንድ ሺሕ እስከ 10 ሺሕ 200 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
በተለይ ከሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ በክልሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በመቋረጡ በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ተስተውሏል ነው የተባለው።
ወደ ክልሉ ይገቡ የነበሩ የኢንዱስትሪ ምርቶች መግባት ካቆሙ አንድ ወር አልፎታል የተባለ ሲሆን፤ እስከዛሬ ነሐሴ 12/2015 ድረስ በጎጃም እና በሸዋ በኩል መንገዱ ዝግ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ የሚገባ ሸቀጣሸቀጥ አለመኖሩ ተመላክቷል።
በዚህም በክልሉ ከተከሰተው ቀውስ ወዲህ በአብዛኛው ቦታዎች በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን መረዳት ተችሏል።
እንዲሁም ወደ ክልሉ ነዳጅ የሚገባው ከጅቡቲ ቢሆንም ከገባ አንድ ወር በላይ መሆኑን እና ነዳጅ የጫኑ ተሽከርካሪዎችም በክልሉ ባለው የጸጥታ ስጋት አፋር ክልል መቆማቸውን አሽከርካሪዎች ጠቁመዋል።
ስለሆነም በነዳጅ እጥረት ምክንያት አብዛኞቹ ተሸከርካሪዎች ሥራ ማቆማቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎችም ከግጭቱ በፊት ከነበረው መደበኛ ክፍያ በእጥፍ ጭማሪ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው።
ተቆጣጣሪ አካል ባለመኖሩም ነጋዴዎችም ይሁን አሽከርካሪዎች እንደፈለጉ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።
በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የአማራ ክልል ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢብራሒም መሐመድ፤ “ስብሰባ ላይ ነኝ ምላሽ መስጠት አልችልም” በማለታቸው ምላሻቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን በበኩሉ፤ “በጉዳዩ ላይ የክልሉን ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ ጠይቁ፣ በእኛ በኩል ምላሽ መስጠት አንችልም፡፡” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።



