ቅዳሜ ነሐሴ 13 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ረ/ፕ/ር ጸጋዬ ቱኬ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ብልፅግና ፓርቲ አስታውቋል።
የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አብርሃም ማርሻሎ በትናንትናው ዕለት በክልሉ ሲካሄድ የቆየዉን የግምገማ እና የ 2015 አፈጸጸም ዉይይት መጠናቀቁን በማስመልከት የተላለፉ ዉሳኔዎችን አሳውቀዋል።
በዚህም መሰረት የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚጎዱ ብልሹ አሰራሮች መስተዋሉን ሀላፊዉ አንስተው ጠንካራ ፓርቲ እና የአመራር ውጤታማነት ከመገንባት አንፃር ብልሹ አሰራር፣ ከሌብነት ጋር በተያያዘ የአፈር ማዳበሪያ ስርቆት፣ የሀዋሳ ከተማ ኮንትራት አስተዳደር እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች መስተዋሉን ገልጸዋል።
እኚህን መሰል ብልሹ አሰራሮችን የሚያርም ጠንካራ የግምገማ መድረክ መካሄዱንም አክለዋል።
በግምገማ መድረኩ ላይ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ረ/ፕ/ር ጸጋዬ ቱኬን በሚመለከት በተካሄደ ግምገማ፤ “አመራራቸው ደካማ ነው፣ የአቅም ውስንነት አለባቸው፣ ከፍተኛ ሙስና ውስጥም ገብተዋል” የሚሉ ሀሳቦች መነሳታቸው ተነግሯል።
በተለይም ከተማው አስገነባሁት ካለው የመግቢያ በር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በሚዲያ 90 ሚሊዮን ብር እንደወጣበት ቢነገርም በመሃንዲስ ተጣርቶ ወጪው ከ30 ሚሊዮን እንደማይዘል በግምገማ መድረኩ ላይ መነሳቱ ተሰምቷል።
ከንቲባ ፀጋዬ የግምገማ መድረክ ላይ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ሲገባቸው፤ ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውም ተገልጿል።
በዚህም መሰረት ከንቲባው ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉ የተነገረ ሲሆን፤ በተጨማሪም የሕግ ተጠያቂነት እንደሚረጋገጥባቸዉ የክልሉ መንግሥት ብልፅግና ፓርቲ አስታውቋል።
በሌላ በኩል፤ የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ፕረስ ሰክረታሪ የከንቲባው ለሃላፊነት መነሳት “የተሳሳተ መረጃ እና ሴራ ነዉ” ሲል ገልጾ ነበር።



