የደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል የከባድ መሳሪያ ጥቃት ደረሰበት

በሕክምና ላይ የነበሩ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጿል

0
299

ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ እና አካባቢው ከነሐሴ 19/2015 ጀምሮ በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የደብረታቦር ጠቅላላ ሆስፒታል በከባድ መሳሪያ መመታቱን ሥማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በተኩስ ልውውጡ ሆስፒታሉ በከባድ መሳሪያ መመታቱን ተከትሎ የሕጻናቶች መታከሚያ ክፍል እንዲሁም የአጥንት እና ማዋለጃ ክፍል ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የተገለጸ ሲሆን፤ የሆሰፒታሉ መሰታወት መርገፉንም ሠራተኞቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም በሆስፒታሉ ላይ በአረፈው የከባድ መሳሪያ ድምጽ ደንግጠው በሕክምና ላይ የነበሩ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጠቆሙት ሠራተኞቹ፤ ከእነዚህ ውስጥ ኹለቱ የልብ ህመም ታካሚ ሕጻናት ነበሩ ብለዋል፡፡

ሠራተኞቹ አክለውም፤ ባለፈው እሑድ ምሽት ሦሰት የፖሊስ አባላት ተገድለው ወደ ሆስፒታል መግባታቸውን ጠቁመው፤ በከተማው ሲካሄድ በነበረው ውጊያ የሆሰፒታሉን ዘበኛ ጨምሮ አስከሬን ተሸክመው ሲወጡ የነበሩ ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውንም ተናግረዋል፡፡

በሆስፒታሉ ተኝተው ሲታከሙ የነበሩ ከ12 በላይ ታካሚዎች ሕክምናቸውን አቋርጠው መውጣታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ታማሚዎች ካሉም የደም እና የኦክስጅን እጥረት መኖሩ ተመላክቷል፡፡

በዚህም በከተማዋ ከሳምንታት በፊት ከተደረገው የኹለቱ ኃይሎች ውጊያ በተጨማሪ ባለፉት ቀናት በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች፤ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸው እና ከፍተኛ የንብረት ጉዳት ማጋጠሙን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በደብረታቦር ከተማ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገው የተኩስ ልውውጥ የግልና የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከነሐሴ 19/2015 ጀምሮ እስከ ዛሬ ነሐሴ 23/2015 ድረስ ዝግ መሆናቸውም ተመላክቷል፡፡

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ከደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ደሳለኝ በላቸው ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።

የከተማዋ ከንቲባ “ጥፋተኞች እኛ ስለሆን ዙሪያ ጥምጥም ሳንሄድ ሕዝቡን ይቅርታ እንጠይቅ። ከታጠቁ ኃይሎች ጋርም ድርድር እናድርግ” ማለታቸውን ተከትሎ በመንግስት የጸጥታ አካላት ታስረው መሰንበታቸው ተመላክቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here