ማክሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ያላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ የዲጂታል እውቀታቸውን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ከሜታ (ፌስቡክ) ጋር በጋራ በመሆን ያዘጋጁትና “የዲጂታል ዕውቀት ለሰላም ግንባታ” በሚል ስያሜ ከመላ አገሪቱ የተውጣጡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ፤ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
ዛሬን ጨምሮ ለኹለት ቀናት የሚቆየው ይህ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ ሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የዲጂታል መድረኮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ እድሎች እና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ የማህበራዊ ትስስር ገፆች የሚያወጧቸውን ፖሊሲዎች በአገራት በእኩል ደረጃ ሊተገበሩ ይገባል ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የዜጎቿን የዲጅታል ሚዲያ አጠቃቀም ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነች እንደምትገኝም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የፕሮግራም እና የልማት ዳይሬክተር ሃና ወልደገብርኤል በበኩላቸው፤ መድረኩ ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትቶች የተውጣጡ ተወካዮች አስፈላጊውን የዲጂታል ክህሎት ለማስያዝ የተነደፈ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህም ደህንነቱ የተጠበቀ እና ኃላፊነት የሚሰማው የዲጂታል መድረክ አጠቃቀምን ለማጎልበት እና በመረጃ የተደገፈ፣ ትርጉም ያለው እና አንጸባራቂ ተሳትፎን ለመፍጠር መታሰቡን ገልጸዋል፡፡
ዳሬክተሯ አክለውም፤ “ዲጂታል መድረኮች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተቋማዊ አቅም መለወጥ፣ የሂደቱን ቅልጥፍና ማሳደግ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማሻሻል፣ የአገልግሎታቸውን ጥራት ማሻሻል እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ የገቢ ማስገኛ መንገዶችን ማቅረብ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡” ብለዋል፡፡
የሜታ የምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የሕዝብ ፖሊሲ ዳይሬክተር ሜርሲ ንደጓ፤ የሰላም ግንባታ ጥረቶች እየተጠናከሩ ሲሄዱ፤ እነዚህን ሂደቶች ከማበላሸት ይልቅ ለማሻሻል ዲጂታል መድረኮች ገንቢ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡
“በሜታ የሚጋሩ ይዘቶች ላይ የፖሊስ አተገባበር ልዩነት ያለ የሚመሰለው፤ ይዘቶቹ ባህላዊ እና ከባቢያዊ አውዶች ስለሚኖራቸው ነው፡፡” ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ሜታ ከአተገባበር ጋር “አሉ” የተባሉትን ችግሮች ለመፍታት ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በዛሬው የመጀመሪያ ቀን የውይይት መድረክ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት ማለትም ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግል ዘርፉ፣ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ ተሳታፊዎች የዲጂታል ኃላፊነት የሚሰማው እና ደህንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀምን ለሰላም ግንባታ የማስተዋወቅ ሥራ ላይ ውይይት አድርገዋል።
በነገው ዕለትም መድረኩ ቀጥሎ ‘የእኔ ዲጂታል አለም’ የሚል ስልጠና እንደሚሰጥ የተገለጸ ሲሆን፤ መርሃ ግብሩ ከመላው ኢትዮጵያ ከተመረጡ 40 የሲቪል ማህበራት፣ የክልል ተሳታፊዎች እንዱሁም ከአዲስ አበባ የመጡትን ተሳታፊዎች ጨምሮ እንደሚካሄድ ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና ሜታ፤ የዲጂታል እውቀት በኢትዮጵያ የሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ቁልፍ መሳሪያ እንደሆነ ለማስተዋወቅ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙም በመድረኩ ተመላክቷል።



