ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ለ2016 የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ ከተያዘው ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መካከል እስከ ሰኞ መስከረም 07/2016 ድረስ የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብቻ መሆኑን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጌታቸው ቢያዝን፤ ለ2016 የትምህርት ዘመን ከነሐሴ 23/2015 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የተማሪዎች ምዝገባ እስከ ሰኞ ድረስ የተመዘገቡት ተማሪዎች 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
“የተማሪዎችን የምዝገባ ጊዜ ከነሐሴ 23/2015 እስከ መስከረም 13/2016 ድረስ ነው፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ “በተያዘው ዓመት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ በእቅድ ተይዞ በክልሉ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለው የጸጥታ ሁኔታ አማካኝነት ምዝገባ ያልተካሄደባቸው ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰውም፤ “የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች መቼ ምዝገባ መካሄድ እንዳለበት እየተወያየን ነው፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።
እንዲሁም ለ2016 የትምህርት ዘመን ወደ ክልሉ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን የመማሪያ መጽሐፍት ታትመው መግባታቸውን እና ወደ ትምህርት ተቋማት የማስራጨት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የ2016 የትምህርት ዘመን በክልሉ መስከረም 14/2016 እንደሚጀመር ገልጸው፤ ሆኖም ይመዘገባሉ ከተባሉት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች እስካሁን አለመመዝገባቸውን ጠቁመዋል።
የተጠቀሰው የተማሪዎች ቁጥር ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉትን የሚያጠቃልል ሲሆን፤ የምዝገባ ቀኑ ሊጠናቀቅ ከአራት የማይበልጡ ቀናት ቢቀሩትም እስካሁን የተመዘገቡት ተማሪዎች ከተያዘው ዕቅድ አንጻር 37 በመቶ የሚደርሱት ብቻ መሆናቸው ተመላክቷል።
የተማሪዎች በወቅቱ አለመመዝገብ በክልሉ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር እንደሚያያዝም ተጠቁሟል።



