ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል በጎጃም የተለያዩ አካባቢዎች ከባለፈው ቅዳሜ መስከረም 05/2016 ጀምሮ እስከ ትናንት መስከረም 7/2016 ለተከታታይ ሦስት ቀናት የመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በቀጠለ ግጭት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
በተለይም የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ፍኖተ ሰላምን ጨምሮ ከብር ሸለቆ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በቅርብ ርቅት ላይ በሚገኘው የማንኩሳ ከተማ፣ ጅጋ እንዲሁም ደንበጫ ከተሞችና አካባቢው ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ከነዋሪዎች መረዳት ተችሏል።
በዚህም በፍኖተ ሰላም ከተማ የአንዲት የ14 ዓመት ሕጻን ልጅ እሁድ መስከረም 06/2015 ከርቀት በተተኮሰ የከባድ መሳሪያ ጥይት ተምትታ መሞቷን እና በትናንትናው ዕለት በከተማው በሚገኘው የገብርኤል ቤተክርስቲያን መቀበሯን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ሥሜ እንዳይጠቀስ ያሉ አንድ የከተማዋ ነዋሪ “ቤት ውስጥ ተደብቀን ነው ያለነው ካለንበት ሰፈር ውጭ ስለሞቱ እና ስለቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ማወቅ አልቻልንም።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንዲሁም በግጭቱ ምክንያት በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፤ በፍኖተ ሰላም ከተማ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ድሪም ጌት ሆቴል “በድሮን ሳይሆን አይቀርም” ባሉት ጥቃት ጉዳት እንደደረሰበት ጠቅሰው፤ በከተማው አደባባይ ፊት ለፊት የሚገኘው ዳሞት ሆቴልም በከባድ መሳሪያ ተመትቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ በሚገኙ የአቦ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መመሰጋቸውን ጠቁመውም፤ በከባድ መሳሪያ በታገዘው የተኩስ ልውውጥ የንጹሃን ዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈ እና ንብረታቸው እየወደመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ መብራት እና ውሃ ከጠፋም አራተኛ ቀኑን ማስቆጠሩንም ገልጸዋል፡፡
ከቅዳሜ ዕለት ጀምሮም በአብዛኛው የምዕራብ ጎጃም ከተሞች ውጊያ እና ውጥረት መኖሩ ነው የተገለጸው።
አዲስ ማለዳ በአካባቢው እየተካሄደ ባለው የተኩስ ልውውጥ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆሰፒታል የገቡ ሰዎችን ቁጥር እና የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ በአካባቢው ከሚገኙ የጤና ተቋማት ለማጣራት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን በቀወት ወረዳ ራሳ ቀበሌ እሁድ መስከረም 06/2015 በመከላከያ ሠራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ፤ የአንድ ሲቪል ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ግጭት በመንግሥት አካላት ዘንድ እንደተቋጨ እና ክልሉም ወደመደበኛ እንቅስቃሴው መመለሱ የሚገለጽ ቢሆንም፤ ከሰብዓዊ መብት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከክልሉ ነዋሪዎችና ከሌሎች አካላት የሚሰጡ ምስክርነቶች ይህን አያሳዩም።



