ረቡዕ መስከረም 9 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አልሸባብ በሶማሊያ ሮብ ድሬ በተባለ ቦታ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቢያስብም፤ ሀሳቡ ሙሉ በሙሉ ከሽፎ በመከላከያ ሠራዊት መደምሰሱን የክፍለጦር አዛዥ የሆኑት ኮሎኔል ፈይሳ አየለ ተናግረዋል።
የአልሸባብ ሃይል ሦስት ፈንጂ የጫኑ መኪናዎችን እና 12 ፈንጂ የታጠቁ ታጣቂዎቹን እንዲሁም፤ ከ450 በላይ አሉኝ የሚላቸዉን አባላቱን ለጥፋት ቢያሰልፍም በቀጠናው በሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የጥፋት ሃሳቡን ሳያሳካ መደምሰሱን ኮሎኔል ፈይሳ ተናግረዋል ።
ሻምበል ጥላሁን ደምሴ በበኩላቸው፤ “ምንም እንኳ በርካታ የሠው ሃይል አሠልፎ በሠው እና በተሽከርካሪ ፈንጅ ጠምዶ ጥቃት ለመፈጸም ቢንቀሳቀስም፤ ኹለት ክፍሎች በመናበብ እና በመቀናጀት ለጥፋት የተንቀሳቀሰውን የአልሸባብ ሃይል ቀደምተኝነትን በመዉሰድ ከአፈር ቀላቅለነዋል፡፡” ብለዋል ።
“አሁንም የሽብር ቡድኑ አልሸባብ ያለበት ቦታ ድረስ እግር በእግር በመከታተል እየለቀምነው ነው አልሸባብን በማጥፋት የቀጠናውን ሠላመም እናረጋግጣለን፡፡” ሲሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አልሸባብ እሁድ መስከረም 6/2015 ጧት ላይ በሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት ባኮል በአጀብ ይሄዱ በነበሩ ኹለት የጭነት ተሽከርካሪዎች (ኮንቮይ) ላይ የደፈጣ ጥቃት ማድረሳቸውን የሶማልያ ባልስልጣናት ማስታወቃቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በዚህም የሽብር ቡድኑ ለጥቃቱ ኃላፊነቱ የወሰደ ሲሆን፤ በጥቃቱ 167 ኢትዮጵያውያን ወታደሮችን መግደሉንመ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማወደሙን እንዲሁም በርካታ የጦር መሳሪዎችን መማረኩን አስታውቆ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በሶማሊያ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ ወታደራዊ ኃይል (አትሚስ) በፈረንጆች 2024 ሙሉ ለሙሉ ከሶማሊያ ለቆ ሊወጣ መሆኑን ተከትሎ፤ አልሸባብ ለኢትዮጵያ ስጋት ሆኗል ሲል ዓለም አቀፍ ጥናትና ትንታኔዎች በመስራት የሚታወቀው ዘጀምስ ታውን ፋውንዴሽን ባወጣው ዘገባ መግለጹ ይታወሳል።
አልሸባብ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ዋነኛ ስጋት ሆኖ የቆየ ሲሆን፤ በተለይም በሶማሊያ በሚፈጽማቸው አውዳሚ ጥቃቶች የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ ይታወቃል።



