በጋምቤላ ክልል ከ6 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አላገኙም ተባለ

0
315

ሐሙስ መስከረም 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በጋምቤላ ክልል የባሮ ወንዝ ከልክ በላይ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ የተፈናቀሉ ከስድስት ሺሕ በላይ ሰዎች እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ እንዳላገኙ፤ የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ተወካይ እና የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሳይመን ቲያች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

“የተከሰተው ጎርፍ እስካሁን በቤት እና ንብረት ላይ እንጂ በሰው ሕይወት ላይ ያስከተለው ጉዳት የለም፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ ለተፈናቃዮቹ እስካሁን ድጋፍ ያደረገ አካል አለመኖሩን ተናግረዋል።

“ተጎጂዎች እርዳታ እንዲያገኙ የፌዴራሉን እና የክልሉን መንግሥት እየጠየቅን ነው፡፡ ድጋፍ የሚያደርጉ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችንም እያፈላለግን ነው፡፡” ሲሉም ተደምጠዋል።

ተፈናቃዮቹ ለጊዜው ያረፉት በተለያዩ ትምህርት ቤቶች መሆኑን ጠቅሰው፤ ወቅቱ የትምህርት መጀመሪያ መሆኑ ኹኔታውን እጅግ ውስብስብ እንዳደረገው ገልጸዋል።

ከኹሉም በላይ አሳሳቢው ጉዳይ ተፈናቃዮች በአንድ ላይ በመሆናቸው እንደወባ ላሉ ውሃ ወለድ በሽታዎች እና ለተለያዩ ሕመሞች ሊጋለጡ ይችላሉ ብለዋል።

ከስድስት ሺሕ በላይ የሆኑ ተፈናቃዮችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ የውሃው መጠን እየቀነሰ ባለመሆኑም አስቸጋሪ ኹኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

“የባሮ ወንዝ ሞልቶ በሚያስከትለው ጎርፍ ነዋሪዎችን ሲያፈናቅል ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡” ያሉት ኃላፊው፤ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ ተፈናቃዮቹን ሊመጣ ካለው ውስብስብ ችግር እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው፤ “መስከረም 04/2016 በተከሰተው ጎርፍ ከቤት ንብረታችን ከተፈናቀልን በኋላ ምንም ድጋፍ ባለማግኘታችን በዚህም ለረሀብ እና ለተለያያ ችግሮች ተጋልጠናል፡፡” ብለዋል፡፡

ጎርፉ በተለይም 01፣ 02 እንዲሁም 04 እና 05 ቀበሌዎች የከፋ ጉዳት በማድረሱ፤ ውሃው አሁንም ተፈናቃዮቹ ወዳሉበት ሥፍራ እየተጠጋ በመሆኑ “ከዚህያም ሊያፈናቅለን ይችላል” በሚል ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

“ጎርፉ ከተከሰተ በኋላም እየጣለ ባለው ዝናብ ሳቢያ ውሃው መጠኑ ባለመቀነሱ ወደ ቀያችን በቅርብ የምንመለስ አይመስለንም፡፡” ያሉት ተፈናቃዮች፤ እርዳታ ባለመቅረቡ እጅግ ኣሳሳቢ ኹኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here