ሐሙስ መስከረም 10 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኮሌራ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ እየተባባሰ መምጣቱን ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እንደገለጸው፤ ባለፈው ሳምንት 400 የሚጠጉ አዳዲስ በኮሌራ የተያዙ ሰዎች ወደ ኩመር የኮሌራ ሕክምና ማዕከል የገቡ ሲሆን፤ ይህም በክልሉ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃ መሰረት ከዚያ ቀደም ከነበረው ሳምንታዊ የኮሌራ ተጠቂዎች ጋር ሲነጻጸር በ50 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
የጤና ተቋማት ባለባቸው የምግብ እጥረት የተነሳ ሕሙማኑን ማቆየት እንዳልቻሉ የገለጸው ጽህፈት ቤቱ፤ ይህም የኮሌራ ወረርሽኙን እያባባሰ ነው ብሏል።
የኮሌራ ሕክምና ማዕከሉ በበኩሉ ችግሩን ለመቆጣጠር አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚሻም ገልጾ፤ ብዙ ሰው ማስተናገድ የሚችል በቂ የሰው ኃይል ባለመኖሩ ብዙዎች እየሞቱ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።
የዓለም ጤና ድረጅት የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ ሰባት ክልሎች ከ20 ሺሕ በላይ የኮሌራ ተጠቂዎች አሉ።
ባለፈው ሳምንት የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ 10 ሺሕ ሱዳናዊያን ስደተኞች በተጠለሉበት ኩመር መጠለያ ጣቢያ፤ ዘጠኝ ሱዳናዊያን ስደተኞች በኮሌራ በሽታ እንደሞቱና 395 ሰዎች በበሽታው መታመማቸው መግለጹ ይታወሳል።



