ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

0
191

ማክሰኞ መስከረም 22 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ሱዳን ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል።

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የከባድ መሣሪያ ጥቃቱ የደረሰው፤ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 22/2016 ጠዋት ላይ መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጮቼ ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

የከባድ መሣሪያ ጥቃቱ በኤምባሲው ሕንጻ እና ንብረት ላይ ውድመት ያደረሰ ሲሆን፤ በሰው ላይ ግን ምንም ዓይነት ጉዳት አለመድረሱ ተነግሯል።

በካርቱም አል-አማራት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ባለፉት ወራት በተለያዩ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥቃት እና ዘረፋ እንደተፈጸመበትም ተመላክቷል።

በአገሪቱ እየተካሄደ ባለው ጦርነት አንደኛው ተፋላሚ ወገን የሆነው በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ፤ ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መድረሱን ገልጿል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለጥቃቱ ተቀናቃኙን በጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሐን የሚመራውን የሱዳን ጦር ሠራዊትን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ በኤምባሲው ላይ በተፈጸመው ጥቃት “በሕንጻው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።” ብሏል።

በኤምባሲው ላይ ጥቃቱ ለምን እንደተፈጸመ እስካሁን የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፤ ስለክስተቱ በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ በጄኔራል አልቡርሐን ኃይሎች በኩል የተባለ ነገር የለም።

በዛሬው ዕለት ጠዋት ላይ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ በተጨማሪ በዩናይትድ አረብ ኤምሬት፣ በሩሲያ እና በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲዎችም ላይ ጥቃት መፈጸሙን ዲፕሎማቱ ተናግረዋል።

በሱዳን የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራት ኤምባሲዎች ካርቱምን ለቀው የወጡ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲም መቀመጫውን ገዳሪፍ ወደሚገኘው ቆንስላ በማዘዋወር የዲፕሎማቲክ ሥራውን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here