ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከአሉቶ ላንጋኖ የጂኦተርማል ፕሮጀክት ለሥራ ሲንቀሳቀሱ ባልታወቁ ሰዎች የታገቱ የፕሮጀክቱን ሠራተኞች ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለው እንደሚገኝ አስታውቋል።
ተቋሙ እገታው መፈጸሙ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የታጋቾች ቤተሰቦች ሳይረበሹ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ ሥራ መስራቱን ገልጿል።
በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች እና አባገዳዎች በኩል የታገቱት ሠዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲለቀቁ ለማድረግ በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቋል።
ከአራት ቀን በፊት ከባቱ (ዝዋይ) ከተማ 17 ኪሜ ገባ ብሎ ወደሚገኘው የአሉቶ ጂኦተርማል ፕሮጀክት ሲጓዙ የነበሩ ስድስት ሠራተኞች በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸው በማህበራዊ ሚደያዎች ሲገለጽ የነበረ ሲሆን፤ ታጋቾች ለመልቀቅ ለእያንዳንዱ 10 ሚልዮን ብር በአጠቃላይ 60 ሚልዮን ብር መጠየቁም ተዘግቧል፡፡
በዚህም ተቋሙ ታጋቾች ያሉበትን ኹኔታ ለማወቅና ታጋቾቹን ለማስለቀቅ አንዳችም ጥረት እያደረገ አይደለም የሚል ወቀሳ ቀርቦበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህን አስመልክቶ፤ “በአንዳንድ የማኅበራዊ ትስስር ዘዴዎች የሚሠራጨው መረጃ፤ የተሳሳተ፣ ለታጋች ቤተሰቦች ስሜት ጥንቃቄ ያላደረገ እና ተቋሙ እያደረገ ያለውን ጥረት ከግምት ውስጥ ያላስገባ ሆኖ አግኝተነዋል።” ብሏል፡፡
የታገቱት ሠራተኞች ደህንነት ተጠብቆ ወደቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተቻለውን ኹሉ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡



