“የአፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው” ኢጋድ

0
262

ረቡዕ መስከረም 23 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጣናዊ ትስስራቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላምና እድገት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ኢጋድ አስታውቋል።

18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ትናንት ሲካሄድ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ.ር) በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምን ማረጋገጥ የዕለት ከዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በቀጣናው የሚገኙ አገራት በታሪክና በባሕል የተሳሰሩ እንደመሆናቸው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን ማጠናከር፣ የተፈጥሮ ሃብትን በጋራ ማልማት እና የድንበር ላይ ንግድን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሚኒስትሮቹ ስብሰባ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የድንበር መሬት ጉዳይ አንዱ አጀንዳ መሆኑንም ዋና ጸሐፊው አንስተዋል።

ዋና ጸሐፊው የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ለአገራቱ ሰላም መስፈን እና የጋራ ትብብር ወሳኝ በመሆኑ “የአፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ሊዘጋጅ ነው” ብለዋል።በቀጣናው አገራት የሚዘጋጀው ፍኖተ ካርታ በአፍሪካ ቀንድ ድንበር አካባቢዎች ልማትን ለማፋጠን፣ የድንበር መሬትን ለማልማት፣ የጋራ ራዕይ እና የትብብር ስትራቴጂ ለማዘጋጀት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።

የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ የተገለሉ ማኅበረሰቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማስፈን የላቀ ድርሻ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡

“በአገራቱ መካከል የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የድንበር መሬት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ቁርጠኝነቱ አለ፡፡” ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ ትግበራውን ዕውን ለማድረግ አሳታፊነትን መሠረት ያደረገ ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

18ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳንን በአባልነት አቅፎ ይዟል።

ኢትዮጵያ ከየካቲት 2015 ጀምሮም የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭን በሊቀመንበርነት እየመራች እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here