ከሦስት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች ከተጠለሉበት ውጡ መባላቸው ተገለጸ

0
338

ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከአውራ ጎዳና ከተማ እና አካባቢው ተፈናቅለው በመልካጅሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጠለሉ ከሦስት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች፤ ትምህርት ሊጀመር በመሆኑ ከተጠለሉበት ውጡ መባላቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አውራ ጎዳና ከተማ እና አካባቢው በተፈጠረው የወሰን ግጭት አማካኝነት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመልካጅሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጠለሉ ከሦስት ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች፤ ትምህርት ቤቱ ትምህርት ሊጀምር በመሆኑ ለቀው እንዲወጡ እንደተነገራቸው አውስተዋል፡፡

ይሁንና “ሌላ አማራጭ መጠለያ  ማግኘት ባለመቻላችን ችግር ላይ ወድቀናል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ቤቱ ከተጠለልን አስራ አምስት ቀን አልፎናል ያሉት ተፈናቃዮቹ፤ “እስካሁን በመንግሥትም ሆነ በግብረ ሠናይ ተቋማት በኩል ምንም አይነት ድጋፍ አልተደረገልንም፤ መጥቶ የጠየቀን አካልም የለም፣ የምንበላው አጥተን ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቀናል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ “የመኖሪያ ቀያችን ወዳለበት አውራ ጎደና ለመመለስ ሙከራ ብናደርግም፤ፐየመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው እንዳንሄድ ከልክለውናል።” በማለት አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል “ሊሰበሰብ የደረሰው የጤፍ፣ የማሽላ እና የበቆሎ ሰብልም በእንስሳቶች እየተበላ ነው።” ያሉት ተፈናቃዮች፤ “ልጆቻችንም በርሃብ ምክንያት ለሕመም ተዳርገዋል።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ሲራጅ አሊየ በበኩላቸው፤ “የአውራ ጎዳና አርሶአደሮች ሰብል በእንስሳቶች እየተበላ ነው።” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው ግጭት አማካኝነት መኖሪያ ቀያቸውን ለቀው መፈናቀላቸውን ተከትሎ፤ ሊሰበሰብ የደረሰ የጤፍና የበቆሎ ሰብል በእንሰሳት እየወደመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ ሰብሉ በእንስሳቶች መውደም የጀመረው ከመስከረም 20 እስከዛሬ መስከረም 24/2016 ድረስ መሆኑን ገልጸው፤ “ከአካባቢው ተፈናቅለው በመልካጅሎ ትምህርት ቤት የተጠለሉ ሰዎችም ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል” ነው ያሉት፡፡

በመልካጅሎ ለሚገኙ ተፈናቃዮች እስካሁን ምንም አይነት ድጋፍ ያደረገ አካል አለመኖሩንም ጠቁመው፤ “በትምህርት ቤቱ የተጠለሉትም ተፈናቃዮች ትምህርት ሊጀመር በመሆኑ ከትምህርት ቤቱ ከወጡ ጎዳና ላይ መውደቃቸው አይቀርም።” ብለዋል፡፡

በመሆኑም “የፌደራልና የክልሉ መንግሥት ለተፈናቃዮቹ ትኩረት ሰጥተው አስቸኳይ ድጋፍ ካላደረገ የከፋ ችግር ላይ ይወድቃሉ።” በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here