ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የ2016 የኢሬቻ በዓል በሰላም እሴቱን ጠብቆ እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮ ኃላፊው ሃይሉ አዱኛ በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ “ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ኹሉን ነገር ለፈጠረ አምላክ ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለምንበት በዓል ነው፡፡” ብለዋል፡፡
በዓሉ የምስጋና፣ የአንድነት፣ የወንድማማችነት፣የይቅርታና የብሩህ ተስፋ በዓል እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ክልል፣ የአዲስ አበባና የፌዴራል ጸጥታ አካላት በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
በዓሉ ያለምንም ፖለቲካዊ አመለካከት ልዩነት በአንድነት የሚከበር መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ በበዓሉ ላይ ከአባገዳ ዓርማ ውጭ የትኛውንም አይነት መለያ ይዞ መሄድ እንደማይቻል በመግለጫው አሳስበዋል።
በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱና የኦሮሞ ገዳ ስርዓት አካል በሆነው የኢሬቻ በዓል ላይ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡



