አርብ መስከረም 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአፋር ክልል ለ2016 የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ በዕቅድ ከተያዘው 245 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ውስጥ፤ እስከ አሁን ድረስ የተመዘገቡት 126 ሺሕ ብቻ መሆናቸውን በአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት እና መማር ማስተማር ዳይሬክቶሬት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በክልሉ የመማር ማስተማር ዝግጅት እና የስርዓተ ትምህርት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወልዶ ሀይሠማ፤ በክልሉ በዞን አራት እና በዞን ኹለት አካባቢዎች ተማሪዎች በብዛት የሚገኙበት ቦታ ቢሆንም፣ ወላጆች ልጆቻቸውን እስከአሁን እንዳላስመዘገቡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች የነበሩ ትምህርት ቤቶች፤ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
“በሌላ በኩል የደብተር እና እስኪሪቢቶ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ እና ኅብረተሰቡ የመግዛት አቅም የሌለው በመሆኑ፤ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት የመላክ ፍላጎት የለውም፡፡” ሲሉ አመላክተዋል።
አክለውም፤ የትምህርት መማሪያ ቁሳቁሶችን ለመግዛት አቅም ካለመኖሩ ባሻገር ለመግዛት አቅም ያለው ወላጅ እንኳን ቢኖር፣ በተጠቀሱት ዞኖች ምንም አይነት የመማሪያ ቁሳቁስ በሱቆች ላይ እንደሌለ አውስተዋል፡፡
የፌደራል መንግሥትና ትምህርት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር የገለጹት ወልዶ፤ አሁን ድጋፉ መቀዛቀዙን ጠቁመዋል።
“ምዝገባው አሁንም ይቀጥላል” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ዘግይተው ለሚመጡ ተማሪዎች ያለፋቸው ትምህርት የሚሸፈንበት መንገድ እንዲሁም በክልሉ ካለው ሞቃታማ አየር ጋር ተስማሚ የሆነ ፕሮግራም የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱን አመላክተዋል።
በሌላ በኩል በጦርነቱ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ከወደሙት 65 ትምህርት ቤቶች ዉስጥ አምስቱ መልሶ ግንባታ እንደተደረገላቸው የገለጹ ሲሆን፤ በከፊል ከወደሙት 6 መቶ 94 መሀል 34ቱ ጥገና እንደተደረገላቸው ገልጸዋል።
አሁን ያለው የመማር ማስተማር ሂደት በአብዛኛው በጊዜያዊነት በድንኳን ዉስጥ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸው፤ ለመምህራን እና ተማሪዎች መጻህፍት ጨምሮ ሌሎች ለመማር ማስተማር ሂደት የሚያስፈልጉ መገልገያዎች በበቂ ኹኔታ እንዳልተሟሉላቸው ጠቁመዋል።
ስለሆነም የመማር ማስተማር ሂደቱን በተገቢው መንገድ ለማስኬድ ኹሉም ባለድርሻ አካላት፣ ወላጆችና ማህበረሰቡ የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ትግራይ ክልልን ሳይጨምር ከ7 ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉና በከፊል የወደሙ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶቹ መልሶ ለማቋቋም 51 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ኣንደሚያስፈልግ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።



