ሐሙስ መስከረም 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ማክሰኞ መስከረም 22/2016 ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ የብልጽግና መንግሥት ለተጎጂዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ ሆን ብሎ እንቅፋት እየሆነ ነው ሲል ገልጿል፡፡
በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች ሕዝቡ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋ ክፉኛ መዳከሙን ያወሳው ኦነግ፤ “ለነዚሁ ተጎጂዎች ድጋፍ እንዳይደረግ እንቅፋ እየሆነ ያለው ሥልጣን የጨበጠው ብልጽግና መራሹ መንግሥት ነው።” ሲል በመግለጫው አስነበቧል፡፡
በተለይም በምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ የኦሮሚያ ክፍሎች ያለው ወረርሽን እና ረሃብ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ላይ መድረሱን በመግለጽ፤ ይሁንና የእነዚህን ወገኖች ሕይወት ለመታደግ በመንግሥት በኩል ምንም አይነት ጥረት ሲደረግ አልታየም ብሏል፡፡
“ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም ደጋግመው “አሳውን ለማጥፋት ቅድሚያ ባሕሩን ማድረቅ” ብለው እንደተናሩት፤ ያሉትን በተግባር ላይ በማዋል ከአፈሙዝ የተረፈውን ሕዝባችንን በረሃብ እና በበሽታ እንዲያልቅ ፈርደውበታል።” ሲል ኦነግ ገልጿል፡፡
“ከወራት በፊት በምስራቅ እና ደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ በተለይም ጉጂ እና ቦረና የተለያዩ ቦታዎች ለተከሰተው ድርቅ ሕዝቡ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳያገኝ እና እንዳያገግም እንቅፋ ሲሆን የነበረው ራሱ መንግሥት ነው።” በማለትም ወቅሷል፡፡
“አሁንም በምእራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ እና ኢሉባቦርን በመሳሰሉ ዞኖች ለረሃብ እና ለተለያዩ በሽታዎች የተጋለጠው ሕዝብ ድምጹ እንዳይሰማ በማፈን እና ቀዳዳዎችን ኹሉ በመድፈን በተለይም የተለያዩ መድሃኒቶችን እንዲሁም የእርዳታ እህሎችን ከተከማቹበት እንዳይወጣ ከላይ እስከታች ያለው የአገዛዙ ክንፍ ተናቦ ይህን ሥራ እየሰራ መሆኑን ኦነግ ያምናል።” ብሏል፡፡
አሁን ላይ ሕዝባችን በወባ፣ ኮሌራ፣ ሳንባ፣ ስኳር እና ለሌሎችም በሽታዎች ከቀን ወደ ቀን እንደቅጠል እየረገፈ ነው ያለው ኦነግ፤ “ከዚህ በተጨማሪም በመንግሥት ታጣቂ በየዕለቱ ይገደላል።” በማለት አውስቷል፡፡
ግንባሩ “ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጫለሁ” እንዳለው ከሆነ በምእራብ ወለጋ ዞን በተለይም በቤጊ፣ ቆንዳላ፣ ላሎ አሳቢ፣ መንዲ፣ ነጆ፣ ቦጂ ጮቆርሳ፣ ቦጂ ቢርመጂ እንዲሁም ባቦ ጋምቤልን በመሳሰሉ ወረዳዎች በወባ ወረርሽኝ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡
ከጤና ተቋማት በተገኘ መረጃ መሰረት በምዕራቡ የኦሮሚያ ክፍል በ16 ዞኖች ሥር በሚገኙ 117 ወረዳዎች፣ በቄለም ወለጋ ሥር በሚገኙ 12 ወረዳዎች እንዲሁም፤ በ7 ሰባት ከተማ መስተዳድሮች በሽታው በወረርሽኝ ደረጃ መኖሩን አረጋግጫለሁ ሲል ኦነግ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በተለይም በቤጊ እና ቆንዳላ ወረዳዎች በ36 ቀበሌዎች ከሚኖሩ 345 ሺሕ በላይ ሰዎች መካከል በቆንዳላ ወረዳ ከ36 ሺሕ በላይ የሚሆኑት በበሽታ እና በረሃብ እየተሰቃዩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
በተመሳይይ “በቤጊ ወረዳ በበሽታ እና በረሃብ ከ 86 ሺሕ በላይ ሰዎች መጠቃታቸውን ከተለያዩ ምንጮች አጣርቻለሁ።” ብሏል፡፡
“አሁን ባለው ተጨባጭ ኹኔታ በእነዚህ ወረዳዎች በቀን እስከ 1 መቶ ሰው በረሃብ እና በበሽታ እንደሚሞት እና በአንድ መቃብር ከሦስት እስከ አራት ሰው እንደሚቀበር ከነዋሪዎች አረጋግጫለሁ።” በማለት በመግለጫው አካቷል፡፡
በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለተጎጂዎች ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በቀጠናው ባለው ግጭት ምክንያት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ለቀው መውጣታውን ያወሳው ኦነግ፤ ይህም ችግሩን የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል ብሏል፡፡
በመሆኑም ምግባረ ሠናይ ተቋማት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በአገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ ወገኖች እንዲሁም ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ለእነዚህ ተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው እና ድምጽ እንዲሆኗቸው ግንባሩ ጥሪውን አቅርቧል፡፡



