የአሜሪካ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ ያቋረጠችውን የምግብ እርዳታ ለስደተኞች ብቻ መልሶ ማስጀመሩን አስታወቀ

0
220

አርብ መስከረም 25 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ ያቋረጠውን የምግብ እርዳታ ለስደተኞች ብቻ መልሶ ለማስጀመር መወሰኑን አስታውቋል።

ዩኤስኤአይዲ የእርዳታ እህል አቅርቦቱን የሚጀምረው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለኹሉም የእርዳታ ፈላጊዎች ሳይሆን፤ በአገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ የጎረቤት አገራት ስደተኞች ብቻ መሆኑን ባወጣው መግለጫ አመላክቷል፡፡

የረድኤት ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ የስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መዋቅር ላይ ለውጦችን በማድረጋቸው እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን የገለጸ ሲሆን፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች የምግብ እርዳታን በማጓጓዝ፣ በማከማቸት እና በማከፋፈል ዙሪያ ምንም አይነት ተሳትፎ እንደማይኖረው ስምምነት ላይ በመደረሱ የእርዳታ እህል አቅርቦቱን ላመስጀመር መወሰኑን ገልጿል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ለሚገኙ አንድ ሚሊየን ለሚሆኑ ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሌሎች አከባቢዎች ለመጡ ስደተኞች የሚውል የእርዳታ እህል አቅርቦት እና ክምችት እንደሚኖር አመላክቷል።

ዩኤስኤአይዲ በመግለጫው፣ “የምግብ እርዳታ በሚያስፈልግባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድጋፉ ለታለመላቸው ተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ማረጋገጫ እስክናገኝ ድረስ ተቋርጦ ይቆያል” ያለ ሲሆን፤ የምግብ እርዳታው ቢቋረጥም የጤና እና የአልሚ ምግቦች እርዳታዎችን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦቶች ግን እንደሚቀጥሉ ገልጿል፡፡

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች መካከል ዋነኛ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የእርዳታ አቅርቦት በመጀመሪያ ያቆረጠው በትግራይ ክልል ነበር፡፡

በማስከተልም ከወራት በፊት “በአገሪቱ የሚቀርበው የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን እና በተቀናጀ ኹኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡” በማለት፤ በመላው አገሪቱ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ ማቋረጡን ማስታወቁ ይታወሳል።

የረድኤት ድርጅቱ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በአብዛኛው በምግብ እርዳታ የቀረበ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ በኢትዮጵያ ማድረጉን አስታውቋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here