ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በዚህ ዓመት 200 ሺሕ የቀድሞ ታጣቂዎች አስፈላጊውን የመልሶ ማቋቋም ስልጠና ወስደው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የብሔራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ተሾመ ቶጋ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ወራት የቀድሞ ታጣቂዎች ከሚገኙባቸው የክልል አመራሮች እና የተሃድሶ ፕሮግራሙን በገንዘብ ከሚደግፉ አጋር አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከጥር ወር 2015 ጀምሮ ኮሚሽኑ የቀድሞ ታጋዮችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በአገሪቱ በስምንት ክልሎች በተካሄደው የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት እንቅስቃሴ፤ 371 ሺሕ 971 የሚሆኑት ታጣቂዎች በኮሚሽኑ መለየታቸውንም አስታውሰዋል።
በዚህ ዓመት ከ150 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ሰዎች አስፈላጊውን የመልሶ ማቋቋም ስልጠና ወስደው ከህብረተሰቡ ጋር እንደሚቀላቀሉም ተሾመ ተናግረዋል።
በውጊያው ላይ ለረጅም ጊዜ ሲሳተፉ የነበሩ ታጋዮች የስነ ልቦና ዝግጅት፣ ፖለቲካዊ ግንዛቤ እና ማህበራዊ ማሻሻያ ለማድረግና ለሰላምና ምርታማነት ዝግጁ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ የኹለት ዓመት መርሃ ግብር በመቅረጽ አስፈላጊውን ገንዘብ ለማግኘት ከአለም ዓቀፍ እና ከአገር ውስጥ የልማት አጋሮች ጋር መወያየቱን የተናገሩም ሲሆን፤ ሥራውን ለማከናወን የሚያግዙ ፕሮጀክቶችን መቅረጹን አስረድተዋል፡፡
አክለውም ለቀድሞ ታጋዮች የማገገሚያ ማዕከላት ግንባታ መጓተትና የስልጠና ሰነዶች ዝግጅት መጓተቱን የገለጹት ሲሆን፤ በቀጣይ ይህንን እውን ለማድረግ ኮሚሽኑ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ከመከላከያ ሚኒስቴር እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ አምስት ትላልቅ ማዕከላትን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
እያንዳንዱ ማዕከል አምስት ሺሕ የቀድሞ ታጣቂዎችን ያስተናግዳል ያሉት ተሾመ፤ ማዕከላቱ የስልጠና ክፍሎች፣ የመኝታ ክፍሎች የሕክምና፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የመመገቢያና ሌሎች መገልገያዎችን ያሟሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለያዩ የመልሶ ማቋቋም መርሃ ግብሮች ታጋዮቹን ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል እቅድ እንዳለም በመግለጽ፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተነሱ 50 ሺሕ የቀድሞ ታጣቂዎችም በፕሮግራሙ እንደሚካተቱ ጠቁመዋል።
ኮሚሽነሩ ለሪፎርም መርሃ ግብሩ ስኬት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንየገለጹ ሲሆን፤ የልማት አጋሮች አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቃል የተገባው ገንዘብ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ለኮሚሽኑ ተደራሽ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኮሚሽኑን ተልዕኮ በተለያዩ መንገዶች ከግብ ለማድረስ የከገር ውስጥ ሲቪል ማህበራት፣ ባለሃብቶች እና ሌሎችም በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።



