የተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ምርመራ አበቃ

0
151

ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የተባበሩት መንግሥታት ድረጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽን፤ ሪፖርቱን ጥቅምት 2/2016 ይፋ በማድረግ የሥራ ጊዜውን አብቅቷል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተካሄደው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም፤ አሁንም ከባድ የመብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ፤ በጦርነቱ በኹሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የሚባሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር የተቋቋመው ኮሚሽን፤ የሥራ ዘመኑ እንዲራዘም የጠየቀ አገር ባለመኖሩ ምክንያት የሥራ ጊዜውን እንዲያበቃ መደረጉ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ የምርመራው ጊዜ በዚህ ወር ሲያልቅ እንደሚበተን ተነግሯል።

የኮሚሽኑ ባለሙያዎች በጉባዔው ለምክር ቤቱ ምርመራው እንዲራዘምላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት በደረሰበት የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አሁንም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሙያዎቹ አክለውም፤ “በትግራይ ክፍል የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጋር በመተባበር ሴቶችን እየደፈሩ እና በወሲብ ባርነት እየገዟቸው ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኹለተኛ በሕዝብ ብዛት በያዘው የአማራ ክልልም አዲስ ጦርነት መቀስቀሱን በመግለጽ፤ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ግድያ እና የጅምላ እስራት ስለመኖሩም ሪፖርቶችን ጠቅሰዋል።

የኮሚሽኑ አባል የሆኑት ስቴቨን ራትነር በጉባዔው፤ “ኹኔታው ይበልጥ እየተባባሰ ሊሄድ የሚችልበት በጣም እውነተኛ እና የማይቀር ስጋት አለ፡፡” ያሉ ሲሆን፤ “የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲቀረፍ እና የከፋ አሳዛኝ ኹኔታዎችን መከላከል እንዲቻል ምርመራው እንዲቀጥል” ጠይቀዋል።

ነገር ግን በጉባዔው የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን እንዲራዘም የጠየቀ አንድም አገር ባለመኖሩ፤ የሥራ ጊዜውን እንዲያበቃ መደረጉ ተነግሯል፡፡

በትግራይ ለኹለት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የአውሮፓ አገራት ምርመራውን ከዚህ ቀደም ደግፈው ነበር።

ኢትዮጵያ የኮሚሽኑን ምርመራ ስትቃወም መቆየቷ የሚታወቅ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ምርመራ እንዳያደርጉ ስትከለክል ቆይታለች፡፡ በዚህም “ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው” ስትል ትወቅሳለች። በዚህ ምክንያት ኮሚሽኑ ምርመራውን በኡጋንዳ ካለው ቢሮ ከርቀት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ኮሚሽኑ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ታኅሳስ 8/2014 ባጸደቀው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ሲሆን፤ ምክር ቤቱ መስከረም 27/2015 የኮሚሽኑን የሥራ ዘመን እስከ ጥቅምት 2016 አራዝሟል።

ሦስት አባላት ያሉት ኮሚሽኑ በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 24/2013 ጀምሮ በኹሉም ወገኖች ተፈጽመዋል የሚባሉ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ እና የስደተኞች ሕግጋት ጥሰቶችን የመመርመር ኃላፊነት ተጥሎበት ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ኹለት ሙሉ ሪፖርቶችን አሳትሟል፡፡

በዚህም በመጀመሪያ ሪፖርቱ “በትግራይ ጦርነት ወቅት ኹሉም ወገኖች በደል ፈጽመዋል፣ ጥቂቶቹ የጦር ወንጀል ናቸው” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ወደ ቀጠናው እንዳይደርስ በመገደብ ረሃብን የጦር መሳሪያ አድርጎታል፡፡” ብሎ ነበር።

የኮሚሽኑ ባለሙያዎች ባለፈው ወር ባሳተሙት ኹለተኛ ሪፖርታቸው፤ “ኢትዮጵያ የጀመረችው አገራዊ የሽግግር የፍትህ ሂደት ከአፍሪካ እና ከአለም አቀፍ ደረጃዎች አንጻር የታሰበለትን ግብ አልመታም” ሲሉ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አለም ዓቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን “በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት እና ተያያዠ አሰቃቂ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ የሚያስችል ከፍተኛ ስጋት አለ።” በማለት ባሳለፍነው ሳምንት ያወጣው ሪፖርት፤ “ሃላፊነት የጎደለው እና በመረጃ ያልተደገፈ ውንጀላ ነው።” ሲል መግለጹን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here