ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በትግራይ ክልል በ2012 ከነበሩት 46 ሺሕ በላይ መምህራን ውስጥ አሁን ላይ ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከሥራ ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።
የትምህርት ቢሮው ሀላፊ ዶ/ር ኪሮስ ግዑሽ ከለኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የሰሜኑ ጦርነት የብዙ መምህራንን ሕይወት አመሰቃቅሏል ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የተሰደዱ፣ የተፈናቀሉ፣ አካላቸው የጎደለ እንዲሁም የሞቱ መምህራን መኖራቸውን አንስተው፤ ከ2 ዓመት በላይ ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ሕይወታቸውን ለማትረፍ የተለያዩ ሥራዎች ውስጥ የተሰማሩ መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የተቀሩት መምህራንም ቢሆኑ በጦርነቱ ምክንያት ብዙ የስነልቦና ጉዳትን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ችግር ደርሶባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ የነበረው ጦርነት በትምህርት ዙሪያ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ያሉት ሃላፊው፤ የትምህርት ቤቶች መቃጠል፣ መፍረስና መውደም አንደኛው ሲሆን፤ በሰው ሃይሉ ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀጥሎ የሚነሳ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
በሦስተኛነት የተነሳው ጉዳይ ደግሞ ስርዓተ ትምህርቱ ሲሆን፤ ብዙ ተማሪዎች በእድሜያቸው ልክ ማግኘት ያለባቸውን ትምህርት ባለማግኘታቸው አሁን ላይ 5ኛ ክፍል እና ከዛ በላይ መሆን የነበረባቸው ልጆች ገና የ1ኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በ2012 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ቢወስዱ ምናልባት አሁን ላይ የ4ኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሚሆኑ፤ ከ9 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከ4 ዓመታት በኋላ ባለፈው ሳምንት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መውሰዳቸው የሚታወስ ነው።



