ረቡዕ ጥቅምት 7 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ታምሩ ገምበታን ጨምሮ፤ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው ተሰምቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰሞኑን መሆኑ ተገለጸ ሲሆን፤ ታምሩ ገምበታ ግን ጥቅምት 5/2016 በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡
የምክትል ዳይሬክተሩ ቤት በፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ መበርበሩ የተገለጸ ሲሆን፤ ዛሬ ጥቅምት 7/2016 ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉም መጠቆሙን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ለውጦች (ሪፎርም) የተደረገ ቢሆንም፣ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች በድለላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
አገልግሎቱን በዋና ዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩት ብሩህተስፋ ሙሉጌታ፣ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ፍራኦል ጣፋና ታምሩ ገምበታን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሦስት ወራት በፊት ሐምሌ መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
ተቋሙ ከፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ሲቀርብበት መቆየቱንና ከዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል በሕወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር ሲልኩ ነበር የተባሉ 16 የተቋሙ ሠራተኞች እንዲሁም፤ አምስት በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሥም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡



